በትግራይ ክልል 'ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ አይደለም' የሚሉ አካላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አስበው ነው - ዶክተር ሙሉ ነጋ

66

ጥር 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) "በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ እንዳልሆነ የሚናገሩ አካላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አስበው ነው" ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ተናገሩ።

የፌዴራል መንግሥት በክልሉ የተጠናከረ ሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዶክተር ሙሉ ነጋ ከኢዜአ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን ሲጀምር ለዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ትኩረት በማድረግ ነው።

ነገር ግን የሰብአዊ ድጋፍ ስርጭቱ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይደርስ የጥፋት ቡድኑ እንቅፋት እንደነበረ አስታውሰዋል።

የጥፋት ቡድኑ የጭነት ተሽከርካሪዎችን አውድሞና የቀሩትን ይዞ መጥፋቱን ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩ እህል በሚያጭድበትና በሚሰበስብበት ወቅት የጥፋት ቡድኑ ችግሩን በመፍጠሩም ለሰብዓዊ ቀውሱ መባባስ አንድ ምክንያት መሆኑን አክለዋል።

"በጥፋት ቡድኑ ምክንያት ህዝቡ ያለ መብራትና ውሃ በመቆየቱ ለከፍተኛ ችግር ተዳርጓል" ያሉት ዶክተር ሙሉ፤ የፌዴራል መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ እንዳልሆነ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬም ከእውነት የራቀ መሆኑን ገልጸዋል።

'ድጋፉ እየቀረበ አይደለም' በሚል ሃሰተኛ መረጃ የሚያናፍሱ አካላት የፖለቲካ ትርፍ በመፈለግ የሚፈጽሙት ድርጊት እንደሆነም ጠቁመዋል።

በክልሉ የመብራት፣ የውሃ እና የባንክ አገልግሎቶች በበርካታ አካባቢዎች መጀመራቸውን አንስተው፤ አገልግሎት ባልተጀመረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ደመወዝ ላልተከፈላቸው የመንግስት ሰራተኞች እንዲከፈላቸው እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የትግራይ ክልልን መልሶ በመገንባት ሂደት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ዶክተር ሙሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም