የፊልም ኢንዱስትሪው ራእይ ያላቸው ወጣት ሙያተኞችን እያፈራ ነው

144
አዲስ አበባ ሃምሌ 17/2010 የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ እየተጠናከረና በርካታ ራእይ ያላቸውን ወጣቶች በንቃት እያሳተፈ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ። በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በየዓመቱ በተለያዩ ጭብጦች የሚያዘጋጀው የአጭር ፊልሞች ውድድር የሽልማት ስነ-ስርዓት ትናንት ምሽት ተካሂዷል። "የእኛ ኢትዮጵያ" በሚል  በተዘጋጀው የዘንድሮ ሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ለአገር አንድነት የሚሰሩ ባለራእይ ወጣት ባለሙያዎችን ማፍራት ጀምሯል። ከሰው ልጆች የጥበብና የሳይንስ ፈጠራ መካከል አንዱ የሆነው የፊልም ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ የፖለቲካና ማህበራዊ ፋይዳ ላላቸው ተግባራት እየዋለ እንደሚገኝም አስረድተዋል። የፊልም ፈጠራ ስራዎች የደስታና የተስፋ ምንጭ ከመሆን ባሻገር ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት፣ በህዝቦች መካከል ሰላምና አንድነት እንዲኖር ለማድረግ እንደዚሁም ድምጻቸው የማይሰማ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምጽ በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ ሚኒስትሯ ገልፀዋል። በኢትዮጵያ የፊልም ኪነ-ጥበብ ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም በመገንዘብ የአሜሪካ ኤምባሲ በተለያዩ ጭብጦች በየዓመቱ የሚያደርገው የአጫጭር የፊልም ውድድር የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬነር በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የዘንደሮው "የእኛ ኢትዮጵያ" በሚል የተዘጋጀው ሽልማት የኢትዮጵያ ፊልም ሥራዎች በህዝቦች መካከል መኖር ያለበትን የመከባበርና መቻቻል እሴቶችን በስፋት እንዲያንፀባርቁ ለማበረታታት ነው። ዘንድሮ ለሽልማት የበቁት የፊልም ሥራዎች በአገሪቷ እየመጣ ያለውን አዲስ የነጻነት መንፈስ ወደ ሰላምና ገንቢ ተግባር ለመቀየር እንደዚሁም የአገሪቷን አንድነት ያጎለብታሉ ተብለው የታመነባቸው መሆናቸውን አምባሳደሩ ገልፀዋል። ለሽልማት የበቁት ስራዎች በዘርፉ የፈጠራ ችሎታና ክህሎት የታየባቸው፣ ጥልቅ መልእክት የተስተዋለባቸው፣ ግንዛቤ የሚያዳብሩና የአገሪቷን ባህል የሚያጎለብቱ ሆነው የተገኙት ናቸው። አምባሳደሩ እንዳሉት፤ የዘንድሮው የፊልም ውድድር በአገሪቷ እየታየ ያለውን ለውጥ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። በወደፊት ክዋኔዎች በጎ አስተሳሰብን፣ ቅንነትን፣ ብዝሃነትን፣ የጋራ ትብብርንና አንድነትን በሚያጎሉ ጭብጦች ላይ በሚያተኩሩ ሥራዎች መካከል ውድድር ይካሄዳል ተብሏል። በዘንድሮው ሽልማት 189 ፊልሞች የተወዳደሩ ሲሆን በጥራት፣ ጭብጥ፣ ፈጠራና በመሳሰሉት የፊልም ጥበብ መስፈርቶች የተሻሉ ሆነው የተገኙ ሶስት ፊልሞች ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ አግኝተው ተሸላሚ ሆነዋል። አሸናፊዎቹም የተለያዩ አቅም ያለውን የአፕል ምርት "አይማክ" የተሰኘ ዘመናዊ ኮምፒውተር ተሸልመዋል። በፊልም ውድድሩ ሁለተኛ የወጣው ኃብተገብርኤል አበበ ''በውድድሩ በተሰጠው ሶስት ደቂቃ ውስጥ ኢትዮጵያን ለመግለጽ ቢያስቸግርም የተቻለኝን ጥረት በማድረግ ለአሸናፊነት በቅቻለሁ'' ብሏል። በቀጣይም አንድነትን የሚሰብኩ ጭብጦች ላይ እንደሚሰራ አስተያየቱን ሰጥቷል። በውድድሩ ሶስተኛ የወጣችው ቅዱሳን ታደሰ በአጭር ደቂቃ የኢትዮጵያን አንድነት የሚሰብክ ፊልም ለመስራት ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም የአገር ፍቅርና አንድነትን ለመግለጽ የተቻላትን ሁሉ እንዳደረገች ተናግራለች። ሽልማቱ በቀጣይም ስለ አንድነት፣ ፍቅር፣ ሰላምና የመሳሰሉት ጭብጦች ላይ ለመስራት የበለጠ ያነሳሳል ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች። በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ አስተባባሪነት የሚካሄደው ይህ የፊልም ሥራ ውድድር ዘንድሮ ሲካሄድ ለአራተኛ ጊዜ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም