በአፋር ክልል የተገነባው የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎች መቆያ ዛሬ ይመረቃል

92

ጥር 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የተገነባው የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎች መቆያ ዛሬ ይመረቃል።

የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎች መቆያው ለጅቡቲ ድንበር የቀረበ ሲሆን ዲቼቶ አካባቢ ነው የተገነባው።

የምረቃ መርሃ ግብሩ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት እንደሚከናወን ታውቋል።

ተርሚናሉ ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎች ጅቡቲ ገብተው ጭነው እስኪመለሱ ድረስ ያለውን ጊዜ አገር ውስጥ እንዲቆዩ የሚያስችል መሆኑ ታውቋል።

ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት የጭነት ተሽከርካሪዎች ወረፋ እስከሚደርሳቸው በጅቡቲ ሲቆዩ የሚወጣውን ወጪ የሚያስቀር ይሆናልም ነው የተባለው።

በተጨማሪም የተሽከርካሪ መቆያ ተርሚናሉ የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችን እንግልትና ወጪ ይቀንሳል ተብሏል።

በቀጣይ ሳምንት ደግሞ ግንባታው የተገባደደው የደወሌ ተርሚናል ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የጋላፊ-ኤሊደአር-በልሆ 71 ኪሎሜትር ኮንክሪት አስፓልት መንገድ ፣ የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በአማራጭነት የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችለው የሚሎዲ መገንጠያ-ማንዳ-ቡሬ ኮንክሪት አስፓልት መንገድ እድሳትም ሌላው የምረቃው አካል ነው።

በተጨማሪም አዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚጀምርም ይጠበቃል።

ከዚህ ሌላ የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና የሁሉም ክልሎች መንገድና ትራንስፖርት ዘርፍ አካላት የሚሳተፉበት የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም እንደሚገመግም ከሉኡካኑ ያገኘውን መረጃ በምንጭነት ጠቅሶ ሪፖርተራችን ከሠመራ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም