በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመስኖ ልማትን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው

87

አሶሳ፤ ጥር 12 / 2013( ኢዜአ) ፡-በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተያዘው የበጋ ወቅት የመስኖ ልማትን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ ባበክር ከሊፋ  እንዳሉት በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወቅት በመስኖ እርሻ 40 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዷል፡፡

እስካሁን ግማሽ ያህሉ መሬት በተለያዩ አትክልቶች ለምቷል ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩ በመስኖ እርሻ በተለይም ከአትክልት ብቻ በሄክታር እስከ 20 ኩንታል ማግኝት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

እቅዱን ለማሳካት የሠላም ሚኒስቴር ድጋፍን በመጠቀም ጭምር አራት ነባር መለስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጥገና እና የማጠናከር ሥራ ለማካሄድ  ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ በጀት  መመደቡን ጠቁመዋል፡፡

በመተከል ዞን ቡለን እና ፓዌ ሲካሄዱ የነበሩ ሌሎች ሁለት መለስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ግን በጸጥታ ምክንያት መቋረጡን አመልክተዋል፡፡

በተቋራጮች ድክመት ሥራቸው የጥራት ጉድለት የታየባቸው ደግሞ ጉዳያቸው በህግ እንዲታዩ የተደረገበት አግባብ መኖሩን ሃላፊው አስረድተዋል፡፡

በአሶሳ ወረዳ በመስኖ እርሻ የሚመረት አትክልት የአሶሳ ከተማ ገበያን ፍላጎት በሚገባ እየሸፈነ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የአሶሳ ወረዳ ግብርና ጸህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አታላይ ደረጀ ናቸው፡፡

በ2012  የምርት ዘመን ብቻ በማህበር ተደራጅተው በመስኖ በመሠማራት የተሻለ ገቢ ያገኙ ወጣቶች ከ80 በላይ ባጃጆችን መግዛታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዘንድሮው የበጋ ውቅት መስኖ ልማት  አብዛኛው የወረዳው አርሶ አደር እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን ሃላፊው አመልክተው የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ለመደገፍ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በአሶሳ ወረዳ በመስኖ ከተሠማሩ አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ ሲቲና መንሱር በሰጡት አስተያየት መስኖ እርሻ ከጀመሩ ሶስት ዓመታት እንደሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አትክልት በማምረት በማገኘው ገቢ ኑሮዬን መቀየር ችያለሁ ብለዋል፡፡

የባለሙያ ምክር መተግበራቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸውና ሌሎች ሴቶች በስፋት በመስኖ እንዲሳተፉ የሚያደርጉት ጥረት እንዳለም ገልጸዋል፡፡

ትርጉም- ወላሂ ይህን መስኖ እርሻ ከጀመርኩ ሶስተኛ ዓመቴ ነው፤  በማገኘው ገቢ የቤተሰቤን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የልጆቼን ሕይወት መቀየር ችያለሁ ፤  የግብርና ባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ ማድረጌ ለውጤት አብቅቶኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም