መንግስት በኦነግ ሸኔ እና የጉሙዝ ታጣቂዎች ላይ ጠንካራና ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

104

መተከል፤ ጥር 12/2013(ኢዜአ) የኦነግ ሸኔ እና የጉሙዝ ታጣቂዎች በመተከል ዞን በዜጎች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለመከላከል መንግስት ጠንካራና ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል በበኩሉ ህብረተሰቡ መረጃ በማቀበል የዘመቻው እንቅፋት የሆኑ ግለሰቦችን ማጋለጥ አለበት ብሏል።

ግብረ ሃይሉ በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ የጋሊሳ ቀበሌ ነዋሪዎችና ተጎጂዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድረገዋል።

በውይይቱ ወቅት ነዋሪዎች እንደተናገሩት፤ በድባጤ ወረዳ ጋሊሳ ቀበሌ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻና ሌሎቸም የኢትዮጵያ ብሄሮች በጋራ በመተሳሰብ ኖረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኦነግ ሸኔ እና የጉሙዝ ታጣቂ በሚፈጽሙት ማንነትን መሰረተ ያደረገ ጥቃት የማህበረሰቡ አብሮነት እንዲሸረሸር እያደረጉ ነው ብለዋል።

"አንድ ብሄር አጥፊ ሌላው ፍጹም አልሚ አይሆንም ከሁሉም አጥፊዎች ይኖራሉ" የሚሉት አስያየት ሰጭዎቹ ጥፋተኛን ለይቶ ለህገግ ማቅረብ ግን ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።

መንግስት በታጣቂዎች ላይ ፈጣንና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አለበት የሚሉት ነዋሪዎቹ እኛም ለመተባበር ዝግጁ ነን ብለዋል።

ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈፅሞባቸው ነገር ግን በህይወት የተረፉ ዜጎች አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ እየተደረገላቸው እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።

በጉልበቱ ለፍቶና ደክሞ የሚሰራን አርሶ አደር በማንነት ለይቶ ማጥቃትና ከአካባቢው እንዲፈናቀል የሚሰሩ ቡድኖችን መንግስት ሊያስቆምና እርምጃም ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።

የኦነግ ሸኔ እና የጉሙዝ ታጣቂዎች ጫካ ሆነው ንጹሃንን ሲያጠቁ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሽፍቶቹ ስንቅ አቀባይ የሆኑ ተለይተው ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውም ጠይቀዋል።

መንግስት ህግ ለማስከበር በቂ አቅም ቢኖረውም በመተከል ዞን ለሚፈጸመው ዘግናኝ ጥቃት የሚሰጠው ምላሽ ግን በቂ አይደለም ሲሉም ቅሬታቸውን አንስተዋል።

ለህዝቡ የወገኑ የጉሙዝ ብልጽግና ሃላፊ ሳይቀር በሽፍታው ስለመገደሉ በማንሳት የደገፍነው ብልጽግና ፓርቲ ግን በሽፍታው ላይ ተገቢውን እርምጃ አልወሰደም ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልል ተወካይ የኮማንድ ፖስት አባል አቶ በዙ ዋቅቤካ፤ ኦነግ ሸኔ በመጀመሪያ የጎዳው እታገልለታለሁ ያለውን የኦሮሞን ህዝብ መሆኑን በማንሳት ቡድኑ ከራሱ ጥቅም ውጭ ለሰብዓዊ ፍጡር ደንታ የለውም ብለዋል።

በመሆኑም ማህበረሰቡ ይህን አረመኔያዊ ቡድን ለማጥፋት በጋራ ሆኖ ሊዋጋው ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ተወካይ የኮማንድ ፖስት አባል አቶ በላይ ዘለቀ በበኩላቸው በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ማነነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት የብሔሮች ሳይሆን የማንንም ብሔር የማይወክሉ የተወገደው ህወሃት አስተሳሰብ ቅሪቶች ናቸው ብለዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢስሀቅ አብዱልቃድር፤ ተጎጂዎች በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል።

በቀጣይ ሁሉንም በጋራ የሚያገለግሉ ሚሊሻዎች እንደሚደራጁ ገልጸው፤ህዝቡ ሁሉንም በቅንነት ያገለግላሉ የሚለውን ለይቶ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ መሳሪያ ያላቸው ግለሰቦች በህጋዊ መንገድ እያስመዘገቡ እራሳቸውን መከላከል እንደሚችሉም አስገንዘበዋል።

የመተከል የተቀናጀ ግብረ ሃይል አባል ብርጋዴር ጀነራል አለማየሁ ወልዴ፤ ሰራዊቱ ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍሎ አካባቢውን ከሽፍታው ያፀጸዳዋል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ነገር ግን የጥፋት ቡድኑን አባላት በማጋለጥ በኩል ማህበረሰቡ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ግብረ ሃይሉ የመተከልን የጸጥታና ህግ የማስከበር ስራ ከተረከበ በኋላ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም በድባጤ ወረዳ ዳሊቲ ጋሊሳ ቀበሌ የ74 ንጹሃን ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም