እንደ ጥምቀት ብዙ ሰዎች በአንድ ቦታ ደምቀውና ተውበው የሚያከብሩት አስደናቂ በዓል አይተን አናውቅም - የውጭ አገር ዜጎች

244

አዲስ አበባ፣ ጥር 11/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እንደሚከበረው የጥምቀት በዓል ብዙ ሰዎች በአንድ ቦታ ደምቀውና ተውበው የሚያከብሩት አስደናቂ በዓል አይተው እንደማያውቁ ኢዜአ ያነጋገራቸው በጥምቀት በዓል የታደሙ የውጭ አገር ዜጎች ገለጹ።

የጥምቀት በዓል በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ዛሬ በጃንሜዳ በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በበዓሉ የታደሙ የውጭ አገር ዜጎች በአገራቸው የጥምቀት በዓል የሚያከብሩት የተወሰኑ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድና በመጸለይ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ብዙ ሰዎች በአንድ ቦታ ተሰብስበው በሕብረ ቀለም ደምቀውና ተውበው እንደሆነና የዚህ አይነት የሃይማኖታዊ በዓል አከባበር ከዚህ በፊት ተመልክተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

በአንድ ቦታ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው በዓልን ሲያከብሩ ማየት በጣም የሚያስደስት ነገር እንደሆነም ገልጸዋል።

ሰዎች በዓሉን አስመልክቶ የሚያሰሙት ዝማሬና የሚያሳዩት ሽብሸባ የሚያስደንቅ እንደሆነና የበዓሉን አከባበር ስነ ስርዓት እንደወደዱትም ነው በበአሉ ላይ የታደሙት የተለያዩ አገራት ዜጎች የገለጹት።

ናይጀል ስዊት የተሰኘው እንግሊዛዊ የእኛ እንዲህ ግዙፍ ስነ ስርዓት የለውም፤ እዚህ ግን በትልቁ ነው የሚከበረው። በእንግሊዝ ሰዎች ቤተከርስቲያን ሄደው ጸሎት ያደርሳሉ ግን እዚህ እንዳለው አይነት አይደለም። በሰንበት ይሄዳሉ ሄደው በዚያው ያበቃሉ። እዚህ ያለው የተለየና ግዙፍ ነው።" ሲል ተናግሯል።

ሌላው እንግሊዛዊ ዴቪድ አሊሰን በኣሉ ደማቅና ትልቅ በዓል መሆኑን ገልጿል።

ስፔናዊው አኒባል ቡዌኖ በኣሉ በጣም የሚያምርና በህብረ ቀለም የተሞላ ነው። ሰዎች ያሸበሽባሉ የምስጋና ዝማሬ ያሰማሉ። ጥምቀት ላይ ስታደም የመጀመሪያዬ በመሆኑ በጣም ነው የወደድኩት። እዚህ ያለው የተለየ ነው። የገና በዓልን እናከብራለን ጥምቀትን ግን አናከብርም። እዚህ ያለው በጣም ይለያል ብሏል።

ስፔናዊዋ ሊዲያ ቦሽ ህዝብ ተሰባስቦ ሲያከብር ስመለከት ተደንቄያለሁ። ሰው ተሰብስቦ በዝማሬ ሲያከብር ማየት በጣም ጥሩ ነው።" ሰትል ተናግራለች።

የጥምቀት ተምሳሌትነቱ ተመሳሳይ ቢሆንም ሁልጊዜ ልዩ ስሜት ይፈጥራል ያሉት የውጭ አገር ዜጎቹ የበዓሉ ስሜት መንፈስን የሚያድስ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የጥምቀት በዓል ትልቅ ፌስቲቫልና ለኢትዮጵያ ትልቅ የአደባባይ በዓል እንደሆነም ገልጸዋል።

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በታህሳስ 2012 ዓ.ም በማይዳሰስ የሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም