የጥምቀት በዓል ሐይማኖታዊ አስተምህሮውንና ስነ-ስርአቱን ሳይለቅ ለትውልድ ማሸጋገር ይገባል- የሃይማኖት አባቶች

101

አዲስ አበባ፣ ጥር 11/2013 (ኢዜአ) የጥምቀት በዓል ሐይማኖታዊ አስተምህሮውንና ስነ-ስርአቱን ሳይለቅ ለትውልድ ማሸጋገር እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በየአመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት በአል በመላ አገሪቱ ተከብሯል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በሐይማኖታዊ ክብረ በዓሉ ላይ የታደሙ የሐይማኖት አባቶች በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ በመጥምቁ ዮሃንስ እጅ መጠመቁ ራሱን ዝቅ አድርጎ ትህትናን እና ፍቅርን ለሰው ልጆች ያሳየበትና ያስተማረበት በዓል መሆኑን ያብራራሉ።

ይህም በተለይ ፍጥረታት ፍጹም ቅንነትን፣ መረዳዳትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መተባበርንና አብሮነትን እንዲያዳብሩ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ይላሉ።

የተለያዩ አንድ የሚሆኑበት፣ የተራራቁ የሚቀራረቡበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት ትልቅ በዓል በመሆኑ በዓሉን ከጥላቻና ከመለያየት በመራቅ ማክበር ይገባል ይላሉ።

በመሆኑም ህዝቦች ክርስቶስ ያስተማረውን የፍቅር እና የትህትና አስተምህሮውን መረዳትና መተግበር ይገባቸዋል ብለዋል የእምነቱ አባቶች።

በዓሉ ከሐይማኖታዊ ትውፊቱ ባሻገር ባህላዊ መስተጋብሩም ትልቅ እንደመሆኑ ሐይማኖታዊ ስነ-ስርአቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ትውልዱ ሐይማኖቱን የሚጠብቅ እና የአባቶችንም ትዕዛዝ የሚያከብር እንዲሆንም የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን በመወጣት አስተምህሮውን በትውልዱ ላይ ማስረጽ ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

መጋቢ ሃዲስ አባ ጸጋ ዘአብ እንዲህ የሰበሰበችን ቅድስት ቤተክርስትያን ናት በበአሉ ህዝቡ የተሰበሰበው በክርስቶስ ፍቅር ነው መራራቅ መለያየት ትተን እጅ ለእጅ ተያይዘን መኖር እንዳለብን ነው የሚያመለክተው ብለዋል።

አባ ሃረገወይን አገዘ ሐይማኖት ሁለገብ ነው የስጋንም የነብስንም ድህነት ነው ፤ ሰላም ነው ፍቅር ነው መረዳዳት ነው።" ሲሉ ተናግረዋል።

መላከጸሃይ ሳሙኤል መስመር በበኩላቸው " እኛ ሃላፊነት የተሸከምን ኖላዊ የምንባል እረኞች ታላቅ ሃላፊነት አለብን ተጠምቀን መሄድ ብቻ ሳይሆን የጥምቀትን ውጤት ማሳየት መቻል አለብን" ብለዋል።

የዘንድሮው የጥምቀት በዓልም ከከተራው ቀን ጀምሮ ሐይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም