የጥምቀት በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በድምቀት ተከበረ

82

ጥር 11/2013(ኢዜአ) የጥምቀት በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በደማቅ ሀይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት በሠላም ተከበረ። 

የኢዜአ ሪፖርተሮች  ከየሥፍራው እንደዘገቡት በኦሮሚያ መቱ፣ አዳማ፣ ነቀምቴ፣ ጅማ ፣ በአማራ ባህርዳር፣ ደብረማርቆስ፣ ደብረብርሃን ደሴ እንዲሁም ደቡብ ፣ ሲዳማ ፣ሐረሪ ፣ ጋምቤላና  አፋር ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ ከተሞችና  ድሬዳዋ አስተዳደር  የሚገኙ ታቦታት ትናንት ከመንበራቸው በመንቀሳቀስ  ጥምቀተ ባህር አድረዋል።

ዛሬ ደግሞ ታቦታቱ ባደሩበት ሥፍራ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ሀይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቱ በደማቅ ሁኔታ  በማካሄድ ተከብሯል።


ታቦታቱም በመነኮሳት፣ ካህናት ቅዳሴ፣ ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ዝማሬ፣ በምዕመናን እልልታ ታጅበው ካደሩበት ወደ መንበራቸው ተመለሰዋል። 


በመቱ ከተማ በዓሉን ሲያከብሩ ከነበሩ መካከል ወጣት ወርቅ አለም ታዬ ለኢዜአ እንዳለችው የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ድምቀት ያለውና በርካታ ምዕመናን የተሳተፉበት ነው።


"የጥምቀት በዓል ለኔ ልዩ ቦታ አለው" ያለችው  ወጣቷ የሌላ እምነት ተከታይ ከሆኑ ጓደኞቿ ጋር ጭምር በድምቀት ማክበሯን ተናግራለች።

የጥምቀት በዓል በሲዳማ ክልል ሀዋሳና ይርጋለም ከተማ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር በተገኘበት በሠላም ተከብሯል፤ ታቦታቱ በሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት ታጅበው ወደ ማደሪያቸው ገብተዋል።

በደቡብ ክልል ዲላ፣ አርባምንጭ፣ ወላይታ ሶዶና ሌሎች ከተሞች ትናንት ከከተራው አንስቶ እስከ ዛሬው ድረስ ያለምንም የጸጥታ ችግር መከበሩን ሪፖርተሮቻችን ዘግበዋል።

የጥምቀተ ባህር አካባቢንና ታቦታቱ በሚጓዙባቸው መንገዶች ሁሉ የእስልምና ዕምነት ተከታዮችን ጨምሮ መላው ህዝብ በጋራ በማጽዳትና ታቦታቱ ትናንት ከደብራቸው ወደ ጥምቀተ ባህሩ ሲጓዙም ሆነ ዛሬ ወደ ደብራቸው ሲመለሱ ወጣቶች ሥርዓቱ ሠላማዊ እንዲሆን ሲሰሩ ቆይተዋል።

የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ካለፉት ሁለት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በተለይ በሀዋሳ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የተሳተፈበት ሲሆን ያለምንም የጸጥታ ችግር የዕለቱ ሥነ-ሥርዓት በሠላም ተጠናቋል። 

በሐረሪ ክልል በተከበረው የጥምቀት በዓል ከታደሙት መካከል  አቶ መስፍን አበጋዝ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በተለይም በዘንድሮ የጥምቀት በዓል ሐረር የሠላም  ፣ መቻቻል እና የፍቅር ከተማ መሆኗ ዳግም በተግባር የተረጋገጠበት ነው ብለዋል፡፡


በተለይም የፀጥታ አካላት እና ህብረተሰቡ ተቀናጅቶ በመንቀሳቀስ በዓሉ በሠላም እንዲከበር ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል፡፡


እኛም በበኩላችን ሠላምና ፍቅር እንዲጎለብት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን ብለዋል፡፡

በዓሉ ከባለፈው ዓመት በተለየ መልኩ ደማቅ እና ሠላማዊ ሆኖ መከበሩን የተናገረው ደግሞ ወጣት ፍፁም ታደሰ ነው፡፡


ከዋዜማው ጀምሮ ሙስሊሙና  ክርስትያኑ በዓሉ የተሳካ እንዲሆን በጋራ ሲሰሩ እንደቆዩ ጠቅሶ  ይህም የሁለቱ እምነት ተከታዮች ወንድማማችነት፣  ፍቅርና አንድነት ያጎለበተ መሆኑን ተናግሯል፡፡


የምስራቅ ሀረርጌና ሱማሌ ሀገረ  ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ መርቆርዮስ እንዳሉት በምስራቅ ሀረርጌ እና ሐረር ከተማ የጥምቀት በዓል ዘንድሮ  ሠላም እና ፍቅር የሰፈነበት በዓል ማክበር ተችሏል፡፡

ሙስሊምና ክርስትያኑም  በመተባባርና ወንድማማችነት አክብረውታል፤ ሐረርም የሠላም ፣የፍቅር እና የአንድነት ከተማ መሆኗን በተግባር የተረጋገጠበት በዓል ነው ብለዋል፡፡

በተለይ የክልሉ እና ምስራቅ ሐረርጌ ዞን  የጸጥታ አካላት ፣ወጣቶች እና ሌላም ማህበረሰብ  በዓሉ በሠላም እንዲከበር ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም