በዓላት ሲከበሩ የተቸገሩትን በመደገፍ ሊሆን ይገባል-አቶ አገኘሁ ተሻገር

84

ጎንደር ጥር/2013 (ኢዜአ ) የጥምቀትንም ሆነ ሌሎች በዓላቶችን ስናከብር በተለያየ ምክንያት የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እየተከበረ ነው።

ርዕሰ መስተዳደሩ በጎንደር ከተማ አፄ ፋሲል ጥምቀተ ባህር በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ እንደገለጹት የጥምቀት በዓል ከባህላዊ ክዋኔው ባለፈ የኢትዮጵያ መገለጫ እየሆነ ነው።

"የዘድሮውን በዓል ስናከብር ባላፈው ዓመት በዚሁ ጥምቀተ ባህር በደረሰ ድንገተኛ አደጋ የተሰውቱን፣ በህግ ማስከበር ህይወታቸው ያለፈና በማንነታቸው የተሰውትን ወገኖች በማሰብ ነው" ብለዋል።

እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደግፍና በማገዝ አጋርነትን በማሳየት ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

ወቅቱ ጠንክራ መተጋገዝና መተሳሰብ የሚጠይቅ ጊዜ እንደሆነ ጠቁመው "ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለመሻገር ትብብር ወሳኝ ነው" ብለዋል።

የጥምቀት በዓል የአንድነት በዓል በመሆኑ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን በመጠበቅ በአሸናፊነት ለመዝለቅ የሚደረገውን ጉዞ በሚያጠናክር አግባብ መከበር እንዳለበት ገልጸዋል።

"በጎንደር ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ አግባብ እየተከናወነ ያለው የጥምቀት በዓል  በመላው አለም የበለጠ እውቅና እንዲኖረው በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።

የጥምቅት በዓል ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ከትውልድ ትወልድ እንዲሸጋገር የክልሉ መንግስት ተገቢውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው "የጥምቀት በዓል ለጎንደርና አካባቢው ህዝብ የማንነቱ መገለጫ ታሪካዊ በዓል ነው" ብለዋል።

"የጥምቅት በዓል መለያየትን በአንድነት፣ ጥልን በፍቅር የሚያስተምርና ወደ ከፍታው እንድንወጣ ትምህርት የሚወሰድበት በዓል ነው " ሲሉም ተናግረዋል።

"የጎንደር ከተማ ልክ እንደ ትናንቱ ዛሬም የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የሰላምና የሃገር ዋልታ ከተማ ናት" ብለዋል።

"ከተማዋ ጥንታዊ ታሪኳን ጠብቃ እንድትቀጥልና በኢኮኖሚ ጠንካራ እንድትሆን የሁሉም ትብብር ይጠይቃል" ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል።

ለከተማዋ ዘላቂ ሰላምና ልማት የከተማ አስተዳደሩ ከህዝቡ ጋር ጠንከራ ትብብር በማድረግ  እንደሚሰራ ከንቲባው አስታውቀዋል።

በአጼ ፋሲል ባህረ ጥምቀት በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከከተማ አስተዳደሩ የመጡ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የእምነቱ ተከታዮች፣በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም