በሰቆጣና ሸረሮ ከተሞች በከተራ በዓል በተከሰተ የኤሌክትሪክ አደጋ የሁለት ወጣቶች ህይወት አለፈ

63

ሰቆጣ  ጥር 11/2013 (ኢዜአ)  በአማራ ክልል በሰቆጣና በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ሸረሮ ከተሞች የከተራ በዓል በሚከበርበት ወቅት በደረሰ የኤሌክትሪክ አደጋ የሁለት ወጣቶች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አሰታወቀ።

የሰቆጣ ከተማ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ኢንስፔክተር ከፍያለው ፅጌ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በከተማው የከተራ በዓል በሚከበርበት ወቅት ታቦታቱን ከፀሃይ የሚከላከል ጥላ ከኤሌክትሪክ ጋር በመነካካቱ  በተከሰተ የኤሌክትሪክ አደጋ የአንድ ወጣት ህይወት ወድያው አልፏል።

በሌሎች ጥላውን በመግፈፍ ላይ በነበሩ ስምንት ወጣቶች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል ።

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ወጣቶች በሰቆጣ ተፈራ ሃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

በበአል ወቅት በቀላል ስህተት ምክንያት የሚፈጠርን ጉዳት ለመቀነስ ታቦታት በሚያልፉበት መንገዶች ዳግም የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከስት ከሚመለከተው ተቋም ጋር እየተስራ መሆኑን ኢኒስፔክተሩ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረሊባኖስ ወረዳ ሸረሮ ከተማ ለጥመቀት በዓል ማድመቂያ ሰንደቅ ዓላማ ለመስቀል የሞከረ የ24 ዓመት ወጣት ህይወቱ ማለፉን የወረዳው ፖሊስ አስታውቋል።

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዘርጋባቸው አበበ ለኢዜአ እንደገለፁት ወጣቱ ፎቅ ላይ ሆኖ የወረወረው ገመድ 33 ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኅይል ማስተላለፊያ ገመድ ላይ በማረፉ በእርጥብ እንጨት ለማንሳት ሲሞክር በኤሌክትሪክ ሀይል ተገፍተሮ ሊወድቅ ችሏል።


ወጣቱ ወደ ሸረሮ ጤና ጣቢያ ቢወሰድም ከ30 ደቂቃ በኋላ ህይወቱ ማለፉን ኮማንደሩ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በበአል ወቅት የሚያደርገው ክንውን ለአካል ጉዳትና ህይወት መጥፋት መንስኤ እንዳይሆን ተገቢ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ኮማንደሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም