'የጥምቀት በዓል ፍቅርንና ትህትናን የምናሳይበት ታላቅ በዓል ነው '' - የሃይማኖት አባቶች

62

አዲስ አበባ ጥር 11/2013 (ኢዜአ) የጥምቀት በዓል ለእምነቱ ተከታዮችም ሆነ ሌሎች የሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርንና ትህትናን ማሳያ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል በመሆኑን የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

ጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በየአመቱ በድምቀት የሚከበር ታላቅ በዓል መሆኑ ይታወቃል።

ዘንድሮም በልዩ ድባብ በአማረ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል።

በአዲስ አበባ በዓሉን ለመታደም ከወጡ የእምነቱ አባቶች መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ እንዳሉት ''በዓሉ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ የሆነው እየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ በማድረግ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ በመጥምቁ ዮሃንስ እጅ መጠመቁን ማሳያ ነው"።

አገልጋይ መምህር ሄኖከ ሃጎስ ክርስቶስ ይህን ሲያደርግ ትህትናን እና ፍቅርን ለሰው ልጆች ሁሉ በግልጽ ያሳየበት በመሆኑ "የሰው ልጆች ሁሉ ከዚህ ፍቅርንና ትህትናን በደንብ ሊማሩ ይገባል" ብለዋል።  

በመሆኑም ትውልዱ በሰላም በፍቅር እና በመተሳሰብ ትህትናን ከአባቶች ሊማር ይገባል ነው ያሉት።

ሌላኛው አባት ርዕሰ ደብርዝራው ወልደኪዳን እንዳሉት ሁላችነም በየተሰማራንበት ሙያ ሁሉ አገልጋይነትን፣ ፍቅርንና አብሮነትን ማሳየት አለብን ብለዋል።

ርዕሰ ደብር አክሊሉ ገብረ ዮሃንስ በበኩላቸው ክርስቶስ ያስተማረው አስተምህሮ ፍቅርን፣ መተሳሰብንና በአንድነት መቆምን በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ለፍቅር እና አብሮነት ትልቅ ስፍራ እንስጥ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የበዓል እቶቻችን ተጠብቀው ለትውልድ እንዲዘልቁና የአገር ሃብት እንዲሆኑ መስራት ይጠበቅብናልም ብለዋል።

የጥምቀት ክብረ በዓል በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡ ይታወቃለ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም