"አምረንና ደምቀን ለምንወጣባቸው ሃይማኖታዊም ይሁን ሌሎች ክብረ በአላት ሰላምና አብሮነታችን ወሳኝ ናቸው"

57

አዲስ አበባ ጥር 11/2013 (ኢዜአ) አምረንና ደምቀን ለምንወጣባቸው ሃይማኖታዊም ይሁን ሌሎች ክብረ በአላት ምንጊዜም ሰላምና አብሮነታችን ወሳኝ ናቸው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጥምቀት በዓል ታዳሚዎች ተናገሩ። 

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል።

ከዋዜማ ጀምሮ በከተራ ደምቆ በማግስቱ በጥምቀት በዓሉ በልዩ ድምቀትና ውበት የሚከናወን መሆኑ ይታወቃል።

በአዲስ አበባ ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው እንዳሉት በአገራችን አምረንና ደምቀን ለምንወጣባቸው ሃይማኖታዊም ይሁን ሌሎች ክብረ በአላት ሰላምና አብሮነታችን ወሳኝነት አላቸው።

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖት እና ትውፊት ባሻገር ኢትዮጵያዊያን በዘውግ፣ በቋንቋ፣ በአካባቢ ሳይለያዩ በአንድነት የሚያከብሩት ልዩ ምልክት መሆኑንም አንስተዋል።

የጥምቀት በዓል በልዩ ድባብ አልባሳትእና ህብረ ቀለማት ደምቆ የሚከበር ልዩ በዓል መሆኑንም አስተያየት ሰጭዎቹ ገልጸዋል።

የዘንድሮው የጥምቀት በዓልም ከከተራው ጀምሮ በልዩ ድምቀት እሴቱን እንደጠበቀ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ በለውጡ ላይ የሚጋረጡ ችግሮችን በአንድናትና በመተባበር ማስወገድ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ዜጎች በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ እንዲሁም በቅንጅት በመስራት ለአገራቸው የበኩላቸውን አስተዋጾ ማበርከት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

ምክንያታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች እርስ በርስ መናቆር ለአገርም ለወገንም ስለማይበጅ አገራችንን በጋራ ልነገነባ ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ህብረተሰቡ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ራሱን ከኮሮና ወረሽኝ በመጠበቅ እና በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ መመሪያዎችን በመተግበር መሆን እንዳለበትም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም