የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል-አቶ አገኘሁ ተሻገር

84

ጎንደር ጥር 10/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የጥምቀት በዓል በሰላም፣ በወንድማማችነትና በመተሳሰብ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የክልሉ ርዕሰ መሰተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር አሳሰቡ።

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ ርዕሰ መሰተዳደሩ መልዕክት አሰተላልፈዋል ።

ርዕሰ መሰተዳደሩ በጎንደር ከተማ በሰጡት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕከት “የዘንድሮ የጥምቀት  በዓል በተለያዩ ሁኔታዎች ውሰጥ ሆነን የምናከብረው ነው” ብለዋል።

የዘንድሮ  የጥምቀት በዓል መንግስት የህግ ማስከበር ሰራውን በተሳካ ሁኔታ ባከናወነበት ማግስት የሚከበር መሆኑ ልዩ እንደሚያደረገው አመልክተዋል።

“ በተለያዩ ክልሎች በማንነታቸው የተፈናቀሉና የተሰዉ ዜጎች  ባሉበት  የችግር ወቅት ላይ  በዓሉ መከበሩም ለህዝባችን ትልቅ ትርጉም አለው “ ሲሉም ተናግረዋል።

በዓሉ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች  የሚከበር መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ “ በጎንደር ከተማ ደግሞ ጥንታዊና ሀይማኖታዊ ይዘቱን ጠበቆ በልዩ ሁኔታ  ይከበራል” ብለዋል።

“መላው የክልሉ ህዝቦች በዓሉን ስናከብር በወንድማማችነትና በእህትማማችነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የምናጠናክረበት ይሆናል” ሲሉም ተናግረዋል።

በዓሉ አንዳችን ለአንዳችን መከታና ጥላ ሆነን የምናከብረው ነው ሲሊም ገልጸዋል።

በዓሉ በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲከበር  ወጣቱ ከጸጥታ ኅይሉ ጎን በመሆን እንዲሰራ ርዕሰ መስተዳደሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም