ተመሳስለው እየተመረቱ ከውጪ የሚገቡ የባህል አልባሳት በስራቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተገለጸ

108

ሶዶ ጥር 10/2013 (ኢዜአ) ተመሳስለው እየተመረቱ ከውጪ የሚገቡ ባህላዊ አልባሳት በሥራቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸው በወላይታ ሶዶ ከተማ በሽመና፣ ባህል አልባሳት ጥልፍና ስፌት የተሰማሩ ግለሰቦች ገለጹ።

በሽመና ስራ እንደሚተዳደሩ የተናገሩት የሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ባፋ ቱማ ለኢዜአ እንዳሉት ካሁን ቀደም በተለያዩ ክብረ-በዓላት የሚለበሰው የሀገር ውስጥ ባህላዊ ልብስ ከውጭ በሚገባ እየተተካ መጥቷል።

በተለይ ከቻይና በማሽን እየተጠለፉ የሚመጡ ጨርቆች የዋጋቸው ዝቅተኛነት አብዛኛው ሰው እንደሚገዛው ተናግረዋል።

በዚህም ከሽመና ሥራ የሚያገኙትን ገቢ ዝቅ ማድረጉን ገልጸዋል።

የሽመና ሥራ አድካሚና ብዙ ቀናት የሚፈጅ በመሆኑ ዋጋውም እንደሚጨምር የተናገሩት አቶ ባፋ ህብረተሰቡ ይህን በመረዳት ለሀገሩ ምርት ተገቢውን ዋጋ መስጠት አለበት ብለዋል።

የሀገር ባህል አልባሳት ሥራው አድካሚ ቢሆንም የተሻለ ገቢ ያገኙበት እንደነበር ያመለከቱት  አቶ ባፋ አሁን ገበያው በመቀዛቀዙ ከውጭ በሚገቡ   ጥልፎች መስራት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በጥልፍና ስፌት ስራ የተሰማራው ልጃቸው አዲሱ ባፋ በበኩሉ በሽመና ከሚሠራው የባህል ልብስ ይልቅ በማሽን የሚታተመው በርካሽ ዋጋ ለገበያ መቅረቡ ስራውን ከባድ እንዳደረገው ተናግሯል።

በፋብሪካ ተመርቶ የሚመጣውን እንደ ጥልፍ በሸማ ላይ ሰፍቶ የመለጠፍ ስራ ቀላል ቢሆንም ከገቢ አንጻር ግን ዝቅተኛ መሆኑን ገልጿል።

 ከቻይና የሚመጡ ጥልፎች በመጠቀም ባህላዊውን በዘመናዊ መልኩ እንደሚሠሩ የተናገሩት ደግሞ በባህል አልባሳት ንግድ የተሰማሩት ሌላው የሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ተረፈ ጌታቸው ናቸው።

ይሄም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሸማቹን ቀልብ እየሳበ መምጣቱን ገልጸዋል።

የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ መከበሩን ተከትሎ የተለያዩ ሐይማኖታዊ ቅርፃቅርፆችን አልባሳቱ ላይ በመለጠፍ በሸማቹ ፍላጎት መሠረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

ከሀገር ውስጥ ስሪቱ ጋርም ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ስላለው የተጠቃሚው ቁጥር መጨመሩንና ገበያ ያለው ቢሆንም በጥራት በሽመና የሚሠሩና በእጅ የሚጠለፉ ባህላዊ አልባሳት ቀስ በቀስ ፈላጊ እንዳያጡ ስጋት እንዳደረባቸው ጠቁመዋል።

ይህ ደሞ በሽመናና ጥልፍ ስራ የተሰማሩትን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጎዳ ሸማቹም ሆነ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ለጥምቀት በዓል በየዓመቱ አዲስ ልብስ የመግዛት ልምድ እንዳላቸው የተናገሩት  ወይዘሮ ፅዮን ወልዱ በሰጡት አስተያየት  በውጭ ጥልፎች የሚሠሩ አልባሳት ከዋጋ አንፃር ተመራጭ አድርጓቸዋል ብለዋል።

ሀገር ውስጥ የሚሠራው ባህላዊ የሽመና ስራ ጥራትና ውበት ቢኖረውም ዋጋው የሚቀመሰ ባለመሆኑ የውጭውን ጥልፍ በፈለጉት ዲዛይን አሰርተው እንደሚለብሱ ገልጸዋል።

ሌላኛው የሶዶ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ኢየሩሳሌም ተፈራ በበኩላቸው የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓት ያለው እንደሆነና ሁሉም ከውጭ ምርቶች ይልቅ የሀገር ውስጥ የሀበሻ አልባሳት ጎልተው ይታዩበታል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ባህላዊ አልባሳት የማንነት መገለጫ ጭምር በመሆናቸው ኢትዮጵያውያን ለራሳችን ምርት ተገቢውን ዋጋና ክብር መስጠት አለብን ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የወላይታ ዞን ንግድ መምሪያ ሀላፊ ዶክተር ምስራቅ አብርሀም እንዳሉት ከውጭ ተመሳስለው ተሠርተው የሚገቡ የባህል አልባሳት አገባባቸው ህግን ያልተከተለ በመሆኑ ቁጥጥር የማድረግ ስራ በዋናነት በትኩረት ሊሠራበት ይገባል።

ሆኖም በባህል አልባሳት ሽመናና ስፌት ስራ የተሰማሩትን በማህበር በማደራጀት የገበያ ዕድል የሚያገኙበት አሠራር እየተዘረጋ በመሆኑ ችግሩ እንደሚቃለል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም