በኮሮና ምክንያት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት እየተሰራ ነው -- ቱሪዝም ኢትዮጵያ

51

ባህርዳር ጥር 10/2013 (ኢዜአ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ።

ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከፌዴራል የስራ ዕድል ኮሚሽን ጋር በመተባበር ከአዲስ አበባና ከተለያዩ ክልሎች ለተውጣጡ ከ150 በላይ ለሚሆኑ አስጎብኚዎች በባህርዳር ከተማ ለሶስት ቀን የሰጠው ስልጠና ትላንት ተጠናቋል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም ካሳሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

የቫይረሱን ክስተት ተከተሎ ከ400 ሺህ የሚበልጡ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ባለመምጣታቸው ሀገሪቱ ከዘርፍ ማግኘት የሚገባትን 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ ማጣቷን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በዘርፉ የተሰማሩ አስጎብኚዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች፣ ሆቴል ቤቶችና ሌሎች ባለድርሻዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

የተጎዳውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የማገገሚያ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዘርፉን ፖሊሲ የመከለስና የቱሪዝም ስትራቴጂውን የማዳበር ስራም አየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። 

“በአስጎብኝዎች ላይ የሚነሱ የስነ-ምግባር ችግሮችን ለመቅረፍ ከ150 ለሚበልጡ የዘርፉ ባለሙያዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው” ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሃት በበኩላቸው “የምናስጎበኛቸው የቅርስ እንዲሁም የመስህብ ቦታዎች በባህልና ኪነ-ጥበብ ቢታገዙ ከፍተኛ የገበያ ተቀባይነት ይኖራቸዋል” ብለዋል። 

“የኪነ ጥበብና የባህልን ትስስር ከቱሪዝም ጋር ማቀናጀት የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ከማራዘም ባለፈ ዘርፉ ስትራቴጂ ተጨምሮለትና በበጀት ተደግፎ ቢሰራ ትልቅ ዋጋና ውጤት ሊያመጣ ይችላል” ሲሉም ተናግረዋል።

የቱሪዝም ዘርፉ ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የፌዴራል የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እንዳልክ ታከለ ናቸው።

ኮሚሽኑም ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር በመቀናጀት በ2013 በጀት ዓመት በቱሪዝም ዘርፍ ብቻ ለ110 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

“የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እንደቀድሞው ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ አይደለም” ያለችው ደግሞ የስልጠናው ተሳታፊ ወይዘሪት ኤድና ታየ ነች።

“ለአስጎብኝዎች እየተሰጠን ያለው ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስልጠና በምንሰራው ስራ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረንና አቅማችንን እንድናሳድግ እየረዳን ነው “ ብላለች።

ከስልጠናው የሚገኝ ግንዛቤ በቱሪስቶች ላይ የሚደርስ መዋከብን ለማስቀረት አስተዋጻ እንዳለው አመልክታለች ።

በየዓመቱ የሚከበረውን የከተራና የጥምቀት በዓል አስመልክቶ የሚመጡ ቱሪስቶችን በአግባቡ ተቀብላ ለማስተናገድ መዘጋጀቷን ወይዘሪት ኤድና ገልፃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም