በአማራ ክልል የከተራና ጥምቀት በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን ፖሊስ አስታወቀ

132

ባህርዳር፣ ጥር 10/2013( ኢዜአ) በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የከተራና ጥምቀት በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሰረት ደባልቄ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በዓሉ በሠላም እንዳይከበር የሚፈልጉ ኃይሎች ችግር እንዳይፈጥሩ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

ህዝቡ በተለይም ወጣቱ የፀጥታው ባለቤት ሆኖ እንዲሰራም ቀደም ብሎ በተዘጋጀው የበዓል ዕቅድ ላይ በተደረገ ውይይት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በየደረጃው ያለው የፀጥታ ኃይልም አስፈላጊው ስምሪት ተሰጥቶት በአሁኑ ወቅት ሌት ተቀን ተቀናጅቶ የአካባቢውን ፀጥታ እያስከበረ ይገኛል ብለዋል።

በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶችም በራሳቸው ተነሳሽነት ዝግጅት አድርገው ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የአካባቢያቸውን ፀጥታ በቅንጅት እየጠበቁ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

እስካሁን በሁሉም የክልሉ አካባቢ ሠላምና መረጋጋት መኖሩን የጠቀሱት ኮማንደር መሰረት ታቦታት ወደ ማደሪያቸው ሲሄዱ የሚያርፉበትን ቦታ ወጣቶች በማጽዳት እያመቻቹ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዓሉ በአደባባይ የሚከበር በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ህብረተሰቡ ሠላሙን እርስ በእርሱ በመጠባበቅ በሠላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የነቃ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ለፀጥታው መጠበቅ አጋዥ እንዲሆኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ህዝቡ በዓሉን ሲያከብር ፀጉረ ልውጦችን ሲያይና አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኙ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጥቆማ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም