በጋምቤላ ክልል በኑዌር ዞን ሁለት ወረዳዎችን ከዞኑ ከተማ ጋር ለማገናኘት የተሰራው ድልድይ ለትራፊክ ክፍት ሆነ

78

ጋምቤላ፣ ጥር 9/2013 ( ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን ሁለት ወረዳዎችን ከዞኑ ከተማ ጋር ለማገናኘት በባሮ ወንዝ ላይ በ25 ሚሊዮን ብር ወጪ የተሰራ የብረት ተገጣጣሚ ድልድይ ለትራፊክ ክፍት ሆነ።

ዛሬ ተመርቆ ለአገልገሎት ክፍት የሆነው ድልድይ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ከላሬ ኝንኛንግ በመገንባት ላይ ያለው የ34 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ አካል እንደሆነ ተነግሯል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በምረቃ ስነ- ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ቢሆንም ህዝቡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚውል በቂ መሰረተ ልማት የለውም።

በተለይም የመንገድና የድልድይ መሰረተ ልማት ተነፍጎት በመቆየቱ በሀብቱ መጠቀም ሳይችል መቆየቱን ገልጸዋል።

"አሁንም የጥራትና የፕሮጀክቶች በጊዜ ያለመጠናቀቅ የዘርፉ ማነቆ እየሆኑ ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከቅርብ ጊዜ ችግሩን ለመፍታት በክልሉና በፌዴራል መንግስት ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት ከፌደራል ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በባሮ ወንዝ ላይ በጊዜያዊነት ተገንብቶ ለትራፊክ ክፍት የሆነው ድልድይ የጅካዎና የላሬ ወረዳዎች ህዝቦች የዘመናት ጥያቄን የመለሰ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ተወካይ ኢንጅነር መሰረት ደጀኔ በበኩላቸው በክልሉ በአሁኑ ወቅት የአቦቦ ሜጢ፣ ጋምቤላ ኢሊያ ጨምሮ የአምስት የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ሁለት የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር የጨረታና የዲዛይን ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ከሁለትና ሶስት ዓመታት በኋላ ብዙ የአስፓልት መንገዶች እንደሚኖሩ አክለዋል።

"ፕሮጀክቶች በጥራትና በጊዜ ካለመጠናቀቅ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የባለስልጣኑ የክትትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል" ብለዋል።

ተገጣጣሚ ድልድዩ የመንገዱንና በቋሚነት የሚሰራውን የ260 ሜትር የኮንክሪት ድልድይ ስራ ለማሳለጥ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ድልድዩ 180 ሜትር ርዝመትና ስድስት ሜትር ስፋት እንዳለውም ኢንጂነር መሰረት አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ድልድይ ባለመኖሩ በጀልባ በመሻገር ለተለያዩ ወጪ እና ከጀልባ አፈትልከው በመውደቅ ለተለያዩ ችግር ሲዳረጉ እንደነበር ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም