የተሃድሶ ስልጠና የተሰጣቸው የትግራይ ክልል ተወላጅ ፖሊስ አባላት በክልሉ ስምሪት እንደተሰጣቸው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ

172

አዲስ አበባ፣ ጥር 9 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአጭር ጊዜ የተሃድሶ ስልጠና የተሰጣቸው የትግራይ ክልል ተወላጅ ፖሊስ አባላት በትግራይ ክልል ህዝብን እንዲያገለግሉ ስምሪት መስጠቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የወንጀል መከላከል ዘርፍ የለውጥ ስራዎች ዲቪዥን ሃላፊ ኮማንደር ተስፋዬ ምህረቱ እንዳሉት ሕግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ በክልሉ ሰላምና መረጋት እንዲሰፍን፣ የክልሉን ጸጥታ ተቋማት ለማደራጀትና ቀሪ የጁንታውን አመራሮችን አድኖ ለፍርድ ለማቅረብ እየተሰራ ነው።

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሰላምና ጸጥታን ለማስፈንና ወንጀለኞችን የማደን ተልዕኮ በመከላከያ ሰራዊትና በፌዴራል ፖሊስ የጋራ ተልእኮ በውጤታማነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የህዝቡን ሰላምና የፍትህ ፍላጎት ለማሳካት የክልሉ ተወላጅ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የስራ ስምሪት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

የፖሊስ አባላቱ ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ የአጭር ጊዜ የተሃድሶ ስልጠና እንደተሰጣቸውም  ኮማንደር ተስፋዬ ገልጸዋል።

የፌዴራል ፖሊስ አባላቱ በየአካባቢው ህብረተሰቡ ያጋጠሙትን ችግሮች በፍጥነት በመፍታት ወንጀለኞችንም የማደን ስራ ያከናውናሉ ተብሏል።

ቀደም ሲል በጁንታው አፈና እና የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ሲደናገር የነበረውን የክልሉን ህዝብ በማረጋጋትና ወደ ሰላምና መልካም አስተዳደር ስራ እንዲመለስ ለማስቻል የፖሊሶቹ ሚና ጉልህ መሆኑንም ተናግረዋል።

ስምሪት የተሰጣቸው የፖሊስ አባላትም ግዳጃቸውን በጥንቃቄና በትኩረት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ ፖሊስ አባላቱ መካከል የዲቪዥን አመራር የሆኑት ኮማንደር ፍጹም በህዝብና መንግስት የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ፖሊስ ዋነኛ ተልእኮው ህዝብን ማገልገል መሆኑን ተናግረው በትግራይ ክልል በተሰጣቸው ግዳጅ ሰላምና ጸጥታን በማረጋጋት ህዝባቸውን ለማገልገል እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም