በዳያስፖራው ተሳትፎ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ሊተገበር ነው

106

አዲስ አበባ፣ ጥር 9 ቀን 2013 (ኢዜአ) በዳያስፖራው ተሳትፎ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ሊተገበር መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው የዳያስፖራውን የበጎ አድራጎት ተሳትፎ ለማሳደግ በሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ቀረፃ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲያካሂድ የቆየው አውደጥናት አጠናቋል።

በአውደጥናቱ ከደረጃ በታች ሆነው ትምህርት እየተሰጠባቸው ያሉ የዳስ ትምህርት ቤቶችን የሚያሻሽል ፕሮጀክት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመቅረፅ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።

የፕሮጀክት ቀረፃውን የልማት ማህበራት፣ የትምህርት ቢሮዎችና የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤቶች በጋራ በመሆን የሚያዘጋጁት ይሆናል።

በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በተለያየ የገጠር አካባቢ 40 ያህል ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እቅድ መያዙ ተገልጿል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ እንዳሉት፤ ዳያስፖራው በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የበጎ አድራጎት ስራዎችን አከናውኗል።

ዳያስፖራው እገዛ ከሚያደርግባቸው ዘርፎች ውስጥ የትምህርት ልማት አንዱ መሆኑን ገልፀው፤ ዘርፉን ለማገዝ የታሰቡት ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የአውደጥናቱ ተሳታፊዎች ዳያስፖራው በተለይ በትምህርትና እውቀት ሽግግር ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ማሳደግ እንዳለበት ጠይቀዋል።

ለትምህርት ዘርፍ እንደመጀመሪያ ዙር የዳያስፖራ በጎ አድራጎት ተሳትፎ ማሳደጊያ ፕሮጀክት ቅድሚያ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ዳያስፖራው በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ሳይገድብ ፕሮጀክቱ እንደሚተገበርም ነው የገለጹት።

የድሬዳዋ ዳያስፖራ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አክሊለ ታጠቅ ዳያስፖራው በድሬዳዋ ከተማና አካባቢው በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የበጎአድራጎት ተግባራት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢው አሁንም ቢሆን በዳስ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ህጻናት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚያደርገውን የበጎ አድራጎት ስራ በአግባቡ ለመምራት መታሰቡ መልካም ጅምር መሆኑን ገልጸዋል።

የከፋ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ብርሃኑ ዳያስፖራው በእውቀትና ክህሎት ሽግግር ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሮጀክቱን በተቀናጀ መልኩ በፌዴራል ደረጃ ለመምራትም ስትሪንግ ኮሚቴ የሚቋቋም ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም