ፋሲል ከነማን በገቢ ለማጠናከር የተዘጋጀ የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር ተካሄደ

78

ጎንደር፣ ጥር 9/2013 (ኢዜአ ) የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ክለብን በገቢ ለማጠናከር የተዘጋጀ የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሄደ፡፡ 

'ለፋሲል እንሩጥ'' በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ሩጫ ከ8 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል።

የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ወጣት ሃይለ ማርያም ፈረደ ለኢዜአ እንደገለጸው የሩጫ ውድድሩ መነሻውን ፕላዛ ሆቴል በማድረግ በከተማው በሚገኘው ፒያሳ መስቀል አደባባይ ተጠናቋል።

በውድድሩም መላኩ ሲሳይ፣ አምሳያው መኮንንና ንጉሴ መንግስቴ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ ደጋፊ ማህበሩ ያዘጋጀውን የገንዘብ ሽልማት የከተማው ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙና የአማራ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ በጋራ ሰጥተዋል፡፡

ለስፖርት ክለቡ ማጠናከሪያ በተዘጋጀው የሩጫ ውድድር ከስፖንሰሮችና ከማልያ ሽያጭ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

በሌላም በኩል የጥምቀትን በአል መዳረሻ ምክንያት በማድረግ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የባህል ሳምንት የኪነ ጥበባት ፌስቲቫል የመዝጊያ ስነ-ስርአት ተካሂዷል፡።

በፊስቲቫሉ የጎንደርና አካባቢውን ባህላዊ ትውፊት የሚያንጸባርቁ የባህል አልባሳት ትርኢትና ውዝዋዜዎች እንዲሁም ባህላዊ ጭፈራዎች ለህዝብ ቀርበዋል፡፡

የነገስታት የአለባበስና የጦር ጀግንነት ተጋድሎ፤ ባህላዊ የጋብቻ ስነ-ስርአት፣ የወይዛዝርት ሴቶች የጸጉር አሰራርና የመዋቢያ ባህላዊ የወግ እቃዎች የተከወነባቸው የጎዳና ላይ ትርኢቶችም ታይተዋል፡፡

በባህል ሳምንት ፌስቲቫሉ መዝጊያ ላይ የከተማው አመራሮች፣ ታዋቂ አርቲስቶችና ከያንያን እንዲሁም የከተማው ወጣቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታዳሚ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም