በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አረጋግጠናል-የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የማዕረግ ተመራቂ ተማሪዎች

120

አሶሳ፣ ጥር 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አረጋግጠናል ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የማዕረግ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ለሰባተኛ ጊዜ 2 ሺህ 182 ተማሪዎችን በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽን ሳይንስ ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 99 ውጤት በማምጣት የተመረቀው ወጣት ጫላ በቃሉ ለኢዜአ እንዳለው፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የኮሮናቫይረስ ክስተትን ጨምሮ ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል፡፡

"ፈተና የሌለው ህይወት የለም" ያለው ወጣቱ፤ በችግር ውስጥ ሆኖ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግሯል ፡፡

ፈተናን ተጋፍጦ ማለፍ ለውጤት እንደሚያበቃ ከራሱ የህይወት ተሞክሮ ማረጋገጡን ጠቅሷል።

"ጊዜዬን በአግባቡ መጠቀሜና አቅሜን አሟጥጬ መስራቴ ለውጤት አብቅቶኛል" ያለችው ደግሞ ከዩኒቨርሲቲው የጤና ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 95 ውጤት በማምጣት የተመረቀችው ወጣት አዜብ ሃይሌ ናት፡፡

ያሳለፈችው የትምህርት ሂደት ውጣ ውረድ የተሞላበት እንደነበር አስታውሳ ጠንክራ በመስራቷ ለውጤት መብቃቷን ተናግራለች።

"የተመረቅኩበት ሙያ የሚፈቅደውን ሀላፊነት በመተግበር ህብረተሰቡን ከወቅቱ የኮሮናወረርሽን ለመታደግ ዝግጁ ነኝ" ብላለች፡፡

በዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክት ፕላኒንግ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂው አቶ አስማማው መንገሻ በበኩላቸው በመመረቂያ ጥናታቸው ግኝት መሰረት ለጥናት በመረጧቸው የመንግስት ተቋማት 42 በመቶ ሃብት እንደሚባክን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ የግል ጥቅምን ማስቀደም እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

"ተመራቂ ተማሪዎች ለህዝብ ጥቅም የምንሠራ ከሆነ ከሌብነት በላይ የምንዋጋው የአገር ጠላት የለም" ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም በምረቃ ወቅት ባደረጉት ንግግር ዩኒቨርሲቲው በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በምህንድስናና በከርሰ ምድር ጥናት የልሕቀት ማዕከል ለመሆን አቅዶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2004 ዓ.ም. ስራ የጀመረው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮው ለሰባተኛ ጊዜ ያስመረቃቸው ተማሪዎች ቁጥር 2 ሺህ 182 ሲሆን ከተመራቂዎች መካከል 145ቱ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት የተከታተሉ ናቸው።

ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ደግሞ 732ቱ ሴቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም