ለጥምቀት በአል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ቅድመ ጥንቃቄ ይደረጋል-የጎንደር ከተማ አስተዳደር

68

ጎንደር፣  ጥር/9/2013(ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በጥምቀት በአል የሚታደሙ የእምነቱ ተከታዮችና እንግዶች ከኮቪድ ወረርሽኝ እራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችሉ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የከተማው ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

ገዝተው መጠቀም አቅም ለሌላቸው የበአሉ ታዳሚዎች 400ሺ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በነጻ ለማሰራጨት ዝግጅት ተደርጓል።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ገበያው አሻግሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት የጥምቀት በአሉን ታሳቢ በማድረግ ወረርሺኙን ለመከላከል የሚያስችል በከተማ ደረጃ አንድ የጤና ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

ግብረ ሃይሉ በጥምቀተ ባህሩ ይታደማሉ ተብሎ የሚጠበቁ ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንግዶችና ነዋሪዎች ለኮቪድ ወረርሺኝ እንዳይጋለጡ ማስክ የመጠቀም አስገዳጅ የጥንቃቄ እርምጃ ይወሰዳል፡፡

የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለመተግበር እንዲቻልም ከሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ጋር የጋራ ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱንም ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴርም ግብረ ሃይሉ ለሚያከናውነው አስገዳጅ የማስክ አጠቃቀም የጥንቃቄ እርምጃ የሚውል 400 ሺህ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በእርዳታ መላኩን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎቹ በጥምቀተ ባህሩ ለሚታደሙ አቅመ ደካሞችም በነጻ የሚሰራጭ እንደሆነም ገልፀዋል።

ሚኒስቴሩ በበአሉ ስፍራ ድንገተኛ የጤና ችግር ለሚገጥማቸው ሰዎች የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ የሚሰጥ ዘመናዊ አምቡላስ ከአራት የጤና ባለሙያዎች ጋር በትብብር እንደላከም አስረድተዋል፡፡

መምሪያው በጥምቀተ ባህሩ ቅጥር ግቢ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና መስጫ ጊዚያዊ ጣቢያ ማቋቋሙን ጠቁመው 32 የጤና ባለሙያዎችና 50 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም መመደባቸውን ተናግረዋል፡፡

ወደ ጥምቀተ ባህሩ የሚገቡ ታዳሚዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ለብሰው ከመግባት ጀምሮ እጃቸውን በሳኒታይዘር የሚያጸዱበት ነጻ የሳኒታይዘር አገልግሎትና የማስክ እደላ በመግቢያ በሮች እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ግራና ቀኝም የእጅ መታጠቢያዎች በበቂ መጠን ለምእመናኑ መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል፡፡

“ከኮቪድ-19 ጋር ሆነን የጥምቀት በአልን ርቀትን በመጠበቅና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማክበር እንችላለን” በሚል መሪ ቃልም ለከተማው ህብረተሰብ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ሃላፊው ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም