ምዕመኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ለኮቪድ ተጋላጭ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለበት-የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

90

አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2013 (ኢዜአ) ምዕመኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ። 

የጉባኤው ዋና ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በቫይረሱ የሚያዙና ወደ ጽኑ ህሙማን የሚያመሩ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል። 

በተለይም በዓላትን ተከትሎ በሚካሄዱ ማኅበራዊ ክንዋኔዎች ሕዝቡ መዘናጋት በማሳየቱ ቫይረሱ በርካታ ሰዎችን በማጥቃት ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ነው ያነሱት። 

በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ኅብረተሰቡ ይህንን ቸልተኝነት መድገም የለበትም ያሉት ቀሲስ ታጋይ፤ በመሆኑም ሁሉም የበዓሉ ታዳሚዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። 

በዓሉ  በርካታ ሰዎች የሚታደሙበት በመሆኑ  ሁሉም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) በማንኛውም ሥፍራ  እንዲያደርግም አሳስበዋል።   

ማስክ መግዛት ለማይችሉ የበዓሉ ታዳሚዎች አቅም ያለው ተጨማሪ ማስክ ይዞ እንዲመጣም ምክራቸውን ለግሰዋል።

ጎን ለጎንም የበዓሉ ታዳሚዎች የእጅ ማጽጃ (ሳኒታይዘር) በመያዝ እጅን በተደጋጋሚ በማጽዳት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት። 

ያም ብቻ ሳይሆን ለቫይረሱ ‘ተጋላጭነትን’ ለመቀነስ ሲባል ርቀትን ጠብቆ ሠላምታ መለዋወጥ እንደሚገባም ቀሲስ ታጋይ ገልጸዋል።

በዓሉ የሕዝቦችን አንድነት፣ አብሮነትና የሰላም እሴቶችን በሚያጠናክር መልኩ መከበር እንዳለበትና ለዚህም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።   

በዓሉ የሰላም፣ የጤናና የፍቅር በዓል እንዲሆን ቀሲስ ታጋይ በጉባኤው ስም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።                                     

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ130 ሺ 772 የደረሰ ሲሆን በቫይረሱ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 2 ሺህ 29 ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም