ምክንያታዊ ወጣቶችን መፍጠር ለሀገር ግንባታ ሂደት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ

142

ጊኒር፣ ጥር 9/2013(ኢዜአ ) ምክንያታዊ ወጣቶችን መፍጠር ለሀገር ግንባታ ሂደት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ።

"ምክንያታዊ ወጣቶች ለሀገር ግንባታ ሂደት ወሳኝ ሚና አላቸው!" በሚል መሪ ቃል በምስራቅ ባሌ ጊኒር ከተማ ትናንት ተካሄዷል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ "አንድን ነገር ሲቃወሙም ሆነ ሲደግፉ በምክንያት የሚያምኑ ወጣቶች በሀገረ መንግስት የግንባታ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና አላቸው" ተብሏል።

የውይይቱ ዓላማ ወጣቶች ሀገርን በመገንባትና የመጣውን የለውጥ ፍሬ እንዲያፈራ በማድረግ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን በመረዳት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማስቻል መሆኑም ተመላክቷል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡት የመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶች መካከል  ወጣት ከዲር ኡስማን እንዳለው ወጣቶች በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የነበራቸው ሚና የላቀ ነው።

የመጣውን ለውጥ በማስቀጠል በኩልም  የወጣቱ ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተናግሯል ።

ውይይቱም በሀገር ግንባታ ሂደት የወጣቱን ሚና በማስገንዘብ አስተዋጾው የላቀ መሆኑን አስታውቋል።

"ሀገር በማሻገር ሂደት ውስጥ የወጣቱ ድርሻ የጎላ ነው ተብሎ ከተገለጸልንና ከተረዳን የሚጠበቅብንን ሚና በተገቢው መወጣት የእኛ ሃላፊነት ነው" ብሏል።

ባለፉት ስርዓት ሰፊው የወጣቱ ኃይል በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በሚፈለገው መልኩ ተሳታፊና ተጠቃሚ ባለመሆኑ ሀገርን በመገንባትና በማሻገር ረገድ ውስብስብ ችግሮች ተፈጥረው ነበር" ያለው ደግሞ ወጣት ሀሰን በከር ነው፡፡

ወጣት ሀሰን እንዳለው  በሀገሪቱ በሚካሄዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኩነቶች ውስጥ ወጣቱን  ኃይል ማሰተፍ ሀገሪቷን ለማሻገር ጉልህ ድርሻ  አለው፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች "አሁን ያለው የለውጥ አመራር ወጣቶች በራሳቸው መስዋዕትነት ካመጡት ሁለንተናዊ ድሎች ተቋዳሽና ተሳታፊ እንዲሆኑ  በቅርበት ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ እሸቱ በቀለ ወጣቶች አሁን የተመዘገበው ለውጥ እንዲመጣ ግንባር ቀደም መስዋዕትነት መክፈላቸውን ተናግረዋል።

"ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረውና ፍሬ እንዲያፈራ ወጣቶች ተሳታፊና ደጋፊ እንዲሆኑ ለማስቻል ቀጣይነት ያለው የምክክር መድረክ ይደረጋል" ብለዋል፡፡

የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደም ቃሲም በበኩላቸው "ወጣቶች ከመጣው ለውጥ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ለስራ ያላቸውን አመለካከት በማስተካከል በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት ይሰራል" ብለዋል፡፡

"የምክክር መድረኩም የዚሁ ጥረት አካልና በየደረጃው ቀጣይነት የሚኖረው ነው" ብለዋል፡፡ 

ለአንድ ቀን በተካሄደው መድረክ ላይ የፌዴራሊዝም ስርዓት፣ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደትና ሌሎች የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ፓኬጅ ላይ ያተኮሩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ  ውይይት ተካሄዷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም