ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለአገር ላበረከቱት አስተዋፅኦ በውጭ ከሚኖሩ የሃድያ ዞን ተወላጆች መኪና ተበረከተላቸው

282

ሆሳዕና፣ ጥር 9/2013 (ኢዜአ) በውጭ አገሮች የሚኖሩ የሀድያ ዞን ተወላጆች ለፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ በተለያየ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የ2020 ሞዴል የቤት መኪና በሽልማት አበረከቱላቸው።

ትናንት ማምሻውን በሆሳዕና ከተማ በተካሄደው መርሀ ግብር ላይ የዳያስፖራዎች አስተባበሪ አቶ ክፍሌ ጋሼ እንደተናገሩት፤ ፕሮፌሰር በየነ በአገሪቱ በትምህርት፣ በምርምር፣ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ላቅ ያለ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

በተለይ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማካሄድ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ ካደረጉ ሰዎች አንዱ በመሆናቸው እውቅናና ሽልማት ለመስጠት መነሳሳታቸውን ገልፀዋል።

"ፕሮፌሰሩ ከደርግ ዉድቀት ማግስት ጀምሮ የህወህትን ሴራ በመቃወም በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ሲያከናውኑት የነበረው እልህ አስጨራሽ ትግል ለተተኪው ትውልድ አርዕያ የሚያደርጋቸው ነው" ብለዋል።

በአጠቃላይ በፖለቲካ መስክ እንደ አገር ፈር ቀዳጅ በመሆናቸው የዞኑ ተወላጅ ዳያስፖራዎች ለፕሮፌሰሩ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የተገዛ የ2020 ሞዴል ሃይሁንዳይ መኪና በሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ሽልማቱን የተረከቡት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ለትምህርት ከነበራቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች በጽናት ተቋቁመው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ መምህር ለመሆን መብቃታቸውን ተናግረዋል።

ከደርግ ዉድቀት ጀምሮ ከስራቸው ባሻገር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበርና በትግላቸውም ለውጥ መመልከታቸውን አስታውቀዋል።

የተሰጣቸው እውቅናና ሽልማት በቀጣይ የተሻለ ለመስራት ከባድ ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን በመግለጽ አገራዊ ግዴታቸውን በትጋት እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የታደሙት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ "ፕሮፌሰር በየነ እንደ አገር በተለያየ ዘርፍ ካበረከቱት አስተዋጽኦ አንጻር እውቅናና ሽልማቱ ይገባቸዋል" ብለዋል።

"ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት በራስ ወዳድነትና ከፍተኛ ሴራ በማሴር በህዝቡ ላይ ከፍተኛ በደል ሲያደርስ የነበረው የህወሀት ዘራፊ ቡድንን በመቃወም ፊት ለፊት የተቃወሙ ጀግና ናቸው" ሲሉም አወድሰዋቸዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ከጥቅምና ስልጣን ይልቅ ለህዝብ ነጻነት ቅድሚያ የሚሰጡ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ለህዝብ መልካም በመስራት የፕሮፌሰሩን አርአያነት ማስቀጠል የትውልዱ ኃላፊነት መሆኑንም ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ከጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃሉ።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም