ሀገራዊ ለውጡ ከዳር እንዲደርስ የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ ነው-ምሁራን

63

ባህር ዳር፣ ጥር 9/2013 (ኢዜአ) -በህዝብ ዘንድ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ሃገራዊ ለውጥ ከዳር እንዲደርስ የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ምሁራን አስታወቁ።

''የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓትና ዲሞክራሲ ለህዝቦች መተሳሰብና አብሮነት'' በሚል መሪ ቃል በባህር ዳር ከተማ ህዝባዊ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

በኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ የታየው ለውጥና በለውጡ የገጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ለኢዜአ እንዳሉት በሃገሪቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የህዝቡን ተስፋ ያለመለመና የዓለምን ቀልብ የሳበ የፖለቲካ ለውጥ ተስተውሏል።

"እስርኞችን በመፍታት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ወደ ሃገር በመመለስ፣ ለሚዲያው ነፃነት በመስጠት፣ የኤርትራን ስላም በመመለስ በአጭር ጊዜ ብዙ ለውጦች ታይተዋል" ብለዋል።

"ነገር ግን ለውጡ ከግቡ ሳይደርስ በርካታ እንቅፋቶች ገጥመውት እንደ ሃገር ፈተናዎች እየተስተዋሉ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

ለውጡ ቀጣይ እንዲሆንና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ሚፈለገው ዴሞክራሲ ለመሸጋገር የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም የፖለቲካ ሊህቃንና ምሁራን ከመገፋፋትና ከመጨቃጨቅ ወጥተው በሰከነ መንገድ ቁጭ ብለው በመነጋገር ሀገርና ህዝብ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ትኩረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ አብራርተዋል።

"በፖለቲካ ምህዳሩ ውስጥ የመደራደር፣ የመመካከርና ልዩነትም ቢኖር ለሀገር የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል" ብለዋል።

ህዝቡን የማንቃትና የማስተማር ግንዛቤውን የማሳደግ ስራም መከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ምሁር ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ በበኩላቸው በሃገሪቱ ፈጥነው ሊስተካከሉ የሚገባቸው አደጋዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ የገጠመውን ተግዳሮች ለመሻገር ህዝቡ ካለፉት ተሞክሮ በመውሰድ በአስተውሎ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበት ገልፀዋል።

"ህዝቡ የማንም ፖለቲከኛ አጀንዳ ተሸካሚ መሆን የለበትም" ያሉት ዶክተር ሹመት ከመጥፎ ድርጊቶች መራቅ እንደሚገባውም ጠቁመዋል።

''ቀደም ሲል ህዝቡን ወደ ገደል ይገፉት የነበሩ ፖለቲከኞች እራሳቸው ገደል ሲገቡ እያየን ነው'' ሲሉ ለአብነት ጠቅሰዋል።

''እኛ ምሁራን ባለን እውቀት ልክ ህዝብና ሃገርን ከጥፋት ለመታደግ ሃላፊነታችን መወጣት አለብንም'' ሲሉ አብራርተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለግል ጥቅማቸው ከመሯሯጥ ወጥተው ሃገርን ሊጠቅሙ በሚችሉ አጀንዳዎች ዙሪያ ሊመክሩና መፍትሄ ሊያስቀምጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በህዝባዊ ኮንፈረንሱ ምሁራን፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የፖለቲካ ፓሪት አመራሮች ጨምሮ የተለያዩ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም