የመከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል ከ113 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የበጎ አድራጎትና የልማት ስራ አከናውኗል

105

አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2013 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሰራዊት ከ2005 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ባሉት የስምንት አመታት ጊዜ ውስጥ በትግራይ ክልል ከ113 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የበጎ አድራጎትና የልማት ስራ ማከናወኑን ገለጸ።

የሰራዊቱ የሰሜን እዝ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ተከትሎ ለ21 ዓመታት በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ የአገሩን ህዝብ ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጣና በትግራይ ክልል የህዝቡን ማህበራዊ ችግር ለመቅረፍ የበጎ አድራጎት እና የመሰረተ ልማት ስራዎችን በማስፋፋት ከክልሉ ህዝብ ጎን በመቆም በርካታ ዘርፈ ብዙ ስራ ማከናወኑ ተገልጿል።

እዙ ካናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ውስጥ በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡ ልጆች፣ ለአቅመ ደካሞች፣ የእርከን ስራ፣ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ፣ ትምህርት ቤቶች መስራት፣ የአቅመ ደካሞች ቤት መስራት፣ መንገድ መገንባት፣ ሰብል ማረምና መሰብሰብ እንዲሁም የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት ግንባታ ላይ ሰራዊቱ ተሳትፎ ማድረጉ ተጠቁሟል።

በዚህም በአጠቃላይ 113 ሚሊዮን 102 ሺህ 426 ብር ግምት ያለው የበጎ አድራጎትና የልማት ስራ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የአገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት መረጃ አመልክቷል።

ከራስ በፊት ለህዝብ እና ለአገር ጥቅም የሚለውን ቁልፍ እሴቱን ተግባራዊ በማድረግ ከወር ደመወዙ በማዋጣት ሞልቶ ስለተረፈው ሳይሆን፣ ያለውን ከወገኖቹ ጋር በፍቅር ተካፍሎ የሚበላ ህዝባዊ ሰራዊት በመሆኑ ተግባሩን እንዳከናወነ ተገልጿል።

ሰራዊቱ ከደመወዙ በመቀነስ የሚወደውን ህዝብ በሞት ላለማጣት ሲል ለኮሮናቫይረስ መከላከያ ግብረ ሃይል ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሷል።

የሰሜን ዕዝ ለበርካታ ጊዜ ደም በመለገስ የዜጎችን ህይወት በመታደጉ ረገድ የራሱን የማይተካ ሚና መጫወቱም ተነግሯል።

No photo description available.
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም