አብሮነታችንን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በጋራ መቆም አለብን -ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

121

አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2013 (ኢዜአ) አብሮነታችንን በማጠናከር ለኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት በጋራ መቆም አለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ጥሪ አቀረቡ።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተለያዩ የሀይማኖት አባቶች ጋር በመሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን  የሚገኘውን የታቦት ማደሪያ ስፍራ አጽድተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ በዚህን ወቅት የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ ክብር በዓልነቱ በተጨማሪ ማሕበራዊ ፈይዳውም የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉ የኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊነት እንዲሁም አንድነትና ጥንካሬ ለዓለም ሕዝብ የምንገልጽበት ነው ብለዋል።

ከተለያዩ ኃይማኖት ተቋማት የተወከሉ ምዕመናን በጽዳት መርሃ ግብሩ መሳተፋቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ኃይማኖቶች መካከል ያለውን ትብብር እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

''ስንፎካከር ሳይሆን ስንተባበር እንከበራለን'' ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ ከዚህ አንጻር አንድነታችንንና አብሮነታችንን በማጠናከር የኢትዮጵያን ውድቀት ለሚፈልጉ አካላት በር መዝጋት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አክለውም በዓሉ ሲከበር ከኮሮና ቫይረስ  በመጠንቀቅ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የአዲስ አበባ አገር ስብከት ስራ አስኪያጅ መምህር አካለወልድ ተሰማ በበኩላቸው የኃይማኖት አባቶች ተባብረው የታቦት ማደሪያ ስፍራን ማጽዳታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ልዩነትን መሰረት አድርጎ መከፋፈል ለሀገር እንደማይበጅም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አባል ሼህ መሓመድ ሲራጅ ኡመር በበኩላቸው ኃይማኖት የግል ሀገር ደግሞ የጋራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ኢትዮጵያዊነታችን የአንዳችን መደሰት ለሌላችን ደስታ፤ መከፋታችን ደግሞ ለሌላው ሀዘን መሆን አለበት ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ አንድነታችንን የምትሻበት ጊዜ በመሆኑ ''ሁላችንም አብሮነታችንን በተግባር ማሳየት አለብን'' በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሰላምና አንድነቱ በጋራ መቆም እንዳለበት መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ሕብረት ጠቅላይ ጸሓፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም