እየተገነቡ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ እየሰራን ነው -ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

75

አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2013 (ኢዜአ) በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው ከተማ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለ4ኛ ጊዜ "ለሀገሬ ሰላም ዘብ እቆማለሁ፣ ለመከላከያ ሰራዊት ቅድሚያ እሰጣለሁ!” በሚል መሪ ሀሳብ በጉለሌ ክፍለ ከተማ አዘጋጅነት ተካሂዷል።

በዝግጅቱም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማዋ ስፖርት ኮሚሽነር፣ የአካል ብቃት አሰልጣኞችና የመዲናዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በዚህን ወቅት በመዲናዋ በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ባለመኖሩ ምክንያት ወጣቶች ጎዳናዎች ላይ የተለያዩ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላል ብለዋል።

በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ አካባቢዎች እያስገነባቸው ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በክፍለ ከተማ ደረጃ የተጀመረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴው ወደ ወረዳዎች፣ ብሎክና በቤተሰብ ደረጃ ድረስ እንዲወርድ ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽነር አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው በመዲናዋ ስፖርትን በመጠቀም ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡ የፈረንሳይ ጨፌ ሜዳ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል።

ምክትል ከንቲባዋ የስፖርት ዘርፍ በመደገፍ ረገድ እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።

5ኛውን ከተማ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የአራዳ ክፍለ ከተማ የሚያስተናግድ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም