የክልሉ ዓመታዊ የክለቦች የእግር ኳስ ውድድር ተጀመረ

51

አሶሳ፣ ጥር 09 / 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 13 ክለቦች የሚሳተፉበት ዓመታዊ የእግር ኳስ ውድድር ተጀመረ፡፡

ለአንድ ወር በሚቆየው የወንዶች እግር ኳስ ውድድር በአሶሳና ካማሽ ዞኖች የሚገኙ 13 ክለቦች ይሳተፋሉ፡፡

የመተከል ዞን ክለቦች በጸጥታ ችግር ምክንያት ተሳታፊ አልሆኑም፡፡

የውድድሩ ዓላማ ክልሉን ወክለው በብሔራዊ ሊግ የሚሳተፉ ሶስት አሸናፊ ክለቦችን ማዘጋጀት እንደሆነ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ አብዱልሙኒዬም አደም ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ህብረተሰቡን ማቀራረብ ሌላው የውድድሩ ትኩረት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ስፖርት ማህበራዊ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ አቅምን እንደሚያጠናክር የገለጹት ኮሚሽነሩ ስፖርት ለሁሉም በሚል መርህ ህብረተሰቡን በዘርፉ በባለቤትነት ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክለቦቹ ስፖርተኞች ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸው በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ በውድድሩ እንዲሳተፉ  መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ ሲባል የተመልካቾች ቁጥር እንዲገደብ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ክልሉ የበርካታ የእግር ኳስ ስፖርተኞች መፍለቂያ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ አብዱልሙኒዬም ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁለቱም ጾታዎች በ95 የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች ታቅፈው እየሰለጠኑ የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በመክፈቻ ውድድሩ ቤኒሻንጉል ፖሊስ ኡንዱሉ ወረዳን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ የአሶሳ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የመክፈቻ ውድድሩን ተከታትለውታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም