የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው- መምሪያው

80

ሶዶ፣ ጥር 9/2013 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን ሶስት ወረዳዎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አሸናፊ አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው በሶዶ ዙሪያ፣ ሁምቦና ኦፋ ወረዳ በአምስት ቀበሌዎች ተከስቷል።

መንጋው እስካሁን በሰብል ላይ ምንም ጉዳት አለማድረሱንና አርሶ አደሩ በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ በባህላዊ መንገድ መንጋው እንዳይረጋጋ በመረበሽ የማባረርና የመከላከል ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መንጋው ጉዳት እንዳያደርስ በባህላዊ መንገድ እየተከናወነ ካለው የመከላከል ስራ ጎን ለጎን ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ህብት ቢሮ ጋር በመቀናጀት የኬሚካል ርጭት ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል።

በሶዶ ዙሪያ የዋጭጋ ቡሻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሉቃስ ካልታሶ በበኩላቸው መንጋው ካሁን ቀደም ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው  ህብረተሰቡ ቀደም የነበረውን ልምድ በመጠቀም መንጋውን እየተከላከለ መሆኑን ተናግረዋል።

የአንበጣ መንጋው ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

''መንጋው እንደ አመጣጡ ቢሆን ሰብል አያስተርፍም'' ያሉት በሁምቦ ኮይሻ ጎላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኡኩሞ ታንጋ አሁን ላይ በተለያዩ ባህላዊ መንገዶች መቆጣጠር መቻላቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም