ምጽዋ የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ንግድ ለማስተናገድ ዝግጁ ሆናለች

114
ኤርትራ ሀምሌ 16/2010 ኤርትራ በምጽዋ ወደብ በኩል የኢትዮጵያን ወጪና ገቢ ንግድ ለማስተናገድ ዝግጁ ሆናለች። የወደቡ አስተዳዳሪ  አቶ ላይኔ አስፋሃለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምጽዋ ወደብ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል አስፈላጊ እድሳት ተደርጎለት ዝግጁ ሆኗል። በመጀመሪያው በረራ ወደ ኤርትራ ያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ ወደቡ ያለበትን ሁኔታ ለመጎብኘት ወደ ስፍራው አቅንቶ ነበር። በዚሁ ወቅት የወደቡ አስተዳደሪ ምጽዋ እንደገና የኢትዮጵያን ወጭና ገቢ ንግድ ለማስተናደግ መታደሱን ተናግረዋል። በስፍራው ተግኝተው የነበሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቂ ወደቡ ሁለቱም አገሮች በኢኮኖሚው ረገድ መተጋገዝ የሚችሉበት ትልቅ ዕድል እንዳለው ነው የገለጹት። በስፍራው የተገኙ ባለሃበቶችም ወደቡን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ተናግረው፣ ከረዥም ጉዞና ተጨማሪ ወጭ እንደሚታደጋቸውም አክለዋል። ለሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ደግሞ ልዩ ጥቅም እንደሚኖረው ጠቁመዋል። አቶ ሃብቶም ገብረአምላክ  '' በተገቢው መሳሪያና አገልግሎት ከተሰናዳ ለሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ቅርብ ነው። በመሆኑም ከዋጋ አንጻር ልዩ ጥቅም ይኖረዋል።” አቶ ዮናስ መኮንን ''ወደቡ ገና ትልቅ እድሳት ቢፈልግም ለሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ትልቅ የወደብ አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል፣ በጂቡቲ ወደብ ከሚፈጠረው ወረፋና መጨናነቅም ይገላግለናል።'' የምጽዋ ወደብ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በቅኝ ገዥዎች የተመሰረተ ሲሆን ከአሰብ ቀጥሎ ሁለተኛው የኤርትራ ወደብ ነው። የሁለቱ አገሮች ድንበር እኤአ በ1998 በጦርነት ምክንያት እስከሚዘጋ ድረስም ለኢትዮጵያ ወጭና ገቢ ንግድ ትልቅ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ወደብ እንደሆነ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም