ጠያቂና ምክንያታዊ ወጣት በመፍጠር ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት እሴት ማጎልበት ይገባል

117

ጥር 08 / 2013 (ኢዜአ) ጠያቂና ምክንያታዊ ወጣት በመፍጠር አለመግባባቶችን በውይይትና በሠላማዊ ሙግት የመፍታት እሴትን ማጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ አስተዳደር "የሃገረ መንግስትና የብሔረ መንግስት ግንባታ ለኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ ከወጣት ምሁራን ጋር ተወያይቷል።

የብልጽግና ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ በአገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ ግጭቶች ሲፈጠሩ ዋነኛ ተሳታፊና ሰለባም እየሆነ ያለው ወጣቱ መሆኑን ተናግሯል።

ይህን ለማስቀረት ጠያቂና ምክንያታዊ ወጣት በመፍጠር አለመግባባቶችና የሃሳብ ልዩነቶችን በንግግርና በሠላማዊ ሙግት የመፍታት እሴት ማጎልበት ይገባል ብሏል። 

ውይይቱ ግጭቶችን በሠላማዊ ሙግት የመፍታት እሴት ለማዳበር አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጾ፤ በእውቀት የታገዘ ወጣት መፍጠርና ከወጣቱ ጋር መመካከር ለሠላም ያለው ሚና ጉልህ መሆኑን አክሏል። 

መሰል ውይይቶች በመላ አገሪቷ እንደሚካሄዱ የጠቆመው ወጣት አክሊሉ በዚህም 5 ሚሊዮን ወጣቶችን የመድረስ ግብ እንደተያዘና መድረኩ በየሦስት ወሩ እንደሚቀጥል አስረድቷል።

በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር አቶ ዮናስ ዘውዴ በሃገረ መንግስትና ብሔረ መንግስት ግንባታ የእኔ አገር ነው የሚል ስሜት እንዲፈጠር ሁሉንም ብሄርና ቋንቋ እኩል ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በአገሪቷ እየታየ ላለው ተግዳሮት ምክንያቶች ካሏቸው መካከል የልሂቃን ዋልታ ረገጥ ትርክቶችና ኢትዮጵያ የብዝሃነት አገር መሆኗን መዘንጋትን በዋናነት ጠቅሰዋል።

ምክንያታዊ ወጣት ለመፍጠርና እየታዩ ያሉ ግጭቶችን ለመቅረፍ ብሔራዊ እርቅ ማድረግና የግለሰብና የቡድን መብቶችን ማክበር ተገቢ መሆኑንም አቶ ዮናስ ገልጸዋል።

ወጣቱ ለሕግና ስርዓት ተገዥ ከመሆን ባለፈ በምክንያትና በእውቀት ሊመራ እንደሚገባም በጥናታቸው አመላክተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ዘቢባ ጀማል በሚፈጠሩ ግጭቶች ቀዳሚ ተሳታፊና ተጠቂ ወጣቱ በመሆኑ ለነገሮች ምክንያታዊ እንዲሆን ታስቦ መድረክ መዘጋጁቱ እንዳስደሰታት ገልጻለች።

ወጣት ለይኩን ዘርጋው በበኩሉ መንግስት ወጣቱ ስለ አገሩ ትክክለኛ እውቀት እንዲኖረው መስራትና የተንጋደደ ታሪክ እንዳይከተል ማድረግ እንዳለበት ነው የተናገረው።

ጠያቂና ምክንያታዊ ወጣት ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑንም አክሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም