በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ ኮሮና መከላከል ንቅናቄ ተጀመረ

48

አሶሳ ፤ጥር 08 / 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል "እንድናገለግልዎ ማክስዎን ያድርጉ " በሚል መሪ ሃሳብ ለስድስት ወራት የሚቆይ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ንቅናቄ ዛሬ ተጀመረ፡፡

በተጀመረው የንቅናቄው መድረክ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሃረላ አብዱላሂ  እንዳሉት በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የጤና ስጋት መሆኑ ቀጥሏል፡፡

በሽታው መቼ እንደሚጠፋ የሚያመላክት ምንም መረጃ እንደሌለ አመልክተው በኢትዮጵያ በየቀኑ በሚመረመሩ ሰዎች ቫይረሱ የሚገኝባቸው መጠን እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡

የቫይረሱ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት የህብረተሰቡ መዘናጋት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ለመፍትሔው ቫይረሱ በከፋ ሁኔታ ሳይስፋፋ የሃገሪቱን በሽታ አስቀድሞ መከላከል ፖሊሲን መሰረት በማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ቫይረሱን ለመከላከል የሚያግዙ  ከ30 ሚሊዮን በላይ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ለማሰብሳብ መታቀዱን ወይዘሮ ሰሃረላ ገልጸዋል፡፡

ጭምብሉ በመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደሚሰበሰብ ጠቁመው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለእቅዱ መሳካት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ መሃመድ አልማሂ ህብረተሰቡ ራሱ እና ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠበቅና ህጎችን እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ የሲቪክ ማህበራት፣ መምህራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እና ሌሎችም የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አሰተላልፈዋል፡፡

ከንቅናቄው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ዘላለም አንዱ  በሰጡት አስተያየት የኮሮና ቫይረስ መከላከል አዋጅ ከተነሳ ጀምሮ ህብረተሰቡ ጭንብል  መጠቀም፣ የእጅ ንጽህናውን መጠበቅ ወደ ማቆሙ ደረጃ መድረሱን እና መጨባበጥ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በከተሞች ችግሩ ይብሳል ብለዋል፡፡

በንቅናቄው የተቀመጡ አቅጣጫዎች እንዲተገበሩ ህብረሰቡን ማስተማር ይጠበቅብናል ያሉት አስተያየት ሰጪው  ቫይረሱን ለመከላከል የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በመዘናጋታችን በኮቪድ-19 ለጉዳት እየተዳረግን ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ይድነቃቸው ደሙ ናቸው፡፡

በየቀኑ የሚመረመሩ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ወደ ኮሮና ጽኑ ህሙማን ማዕከል የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር ስለመጨመሩን በመገናኛ ብዙሃን ሲገለጽ መስማታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ንቅናቄው ችግሩን በማቃለል ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያግዛል ሲሉ  አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም