በደቡብ ክልል አቀፍ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው

82

ሶዶ፤ ጥር 8/2013 (ኢዜአ )በደቡብ ክልል የዘንድሮ ክልል አቀፍ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የንቅናቄ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ እንዳሉት አምና በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ 355 ሺህ 654 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል።

በለማው መሬት ላይም በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ1 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ ጠቀሜታ ያላችው ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የተፋሰስ ልማት ስራ የተራቆተና ምርታማነቱ የቀነሰ መሬት መልሶ ማገገም እንደቻለ ገልጸዋል።

በዚህም ምርትና ምርታማነት መጨመር እንደቻለ፣ የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር የውሃ ሀብት ላይም ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ተናግረዋል።

ዘንድሮም ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የተሻለ የአካባቢ ጥበቃና ልማት ተግባራትን ለማከናወን ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

የዘንድሮው ክልላዊ ንቅናቄ "የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ለሁለተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ከጥር 18/2013ዓ.ም. ጀምሮ  ለ30 ቀናት እንደሚቆይና  በዚህም 357 ሄክታር መሬት ይለማል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም