ጥምቀት ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር የሕዝቦች አንድነት ማሳያ ነው

112

አዲስ አበባ ጥር 8/2013 (ኢዜአ) የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ስርዓቱ ባሻገር የሕዝቦች አንድነትና ኢትዮጵያዊነት የሚጎላበት በመሆኑ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆ ማክበር እንደሚገባ ተገለጸ።

ከተራና ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና በዕምነቱ ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል ናቸው፡፡

በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበረው የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ባሕላዊ እሴት ጋር ቁርኝቱ የጠበቀ በመሆኑ ለሕዝቦች አንድነት ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለውም ይነገራል።

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /ዩኔስኮ/ም የጥምቀትን በዓል በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስነት መዝግቦ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ቅርስ አድርጎታል፡፡

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸውም በዓሉ ከዕምነቱ ተከታዮች ባሻገር ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የአንድነት ማሳያ መሆኑን ይገልፃሉ።

በአደባባይ የሚከበር መሆኑ ደግሞ በሃይማኖታዊ ስርዓቱ የማይታደሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በባሕላዊ ክዋኔው መሳተፍ የሚችሉበት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዩ ፅህፈት ቤት የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራሉ።

የጥምቀት በዓል ባሕላዊ ክዋኔዎች ከዕምነቱ ባለፈ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

የተለያዩ አለባበሶች፣ ባሕሎችና ዝማሬዎች በተለያዩ ቋንቋዎች መቅረባቸው የሕዝቡን አንድነትና ቤተ-ክርስቲያኗም የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እናት ለመሆኗም ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዓሉ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ጭፈራዎችና ልዩ ልዩ ክዋኔዎች እንደሚንጸባረቁበት የገለጹት አቶ አለማየሁም እነዚህ የሕዝቦችን አንድነት ከማጠናከር አንጻር ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የአገርን ገጽታ በመገንባት፣ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳላቸው አስረድተዋል።

በበዓሉ ላይ የሚስተዋለው የሕዝቦች አብሮነትና አንድነት ከበዓሉ በኋላም እርስ በእርስ ለመተሳሰብና ለመረዳዳት መሰረት እንደሚጥል ነው የገለጹት።

ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊም ጥምቀት ሁሉም ሰው ያለአንዳች ልዩነት የሚያከብረው የመተሳሰብ፣ የአንድነትና የመረዳዳት በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጥምቀት በዓል ከዕምነቱ ተከታዮች ባሻገር የሌሎች ዕምነቶች ተከታዮችና በርካታ ቱሪስቶች የሚታደሙበት ጭምር መሆኑንም ነው ያወሱት፡፡

"ጥምቀት የአንድነት መገለጫ ነው" ያሉት ሊቀ-ጳጳሱ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ማክበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ብፁዕነታቸው ወጣቶች ከበዓሉ ቀደም ብሎ ጥምቀተ ባሕሩን ከማፅዳት ጀምሮ ታቦታት የሚያልፉባቸውን መንገዶች የማፅዳት፣ የማስዋብና የማስተናበር ስራቸውን እንደወትሮው እንዲያከናውኑም ጠይቀዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ የተጎዳው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲያገግም ኅብረተሰቡ የከተራና የጥምቀት በዓላትን ሲያከብር ራሱን ከበሽታው በጠበቀ መልኩ እንዲሆንም ጥሪ ቀርቧል።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቱ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋጾ እንደሚያስፈልግም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም