ለሀገሪቱ ሁለንታናዊ ግንባታ ክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር ተቀናጅቶ ይሠራል - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

76

አዳማ ጥር 8/2013 (ኢዜአ) ለሀገሪቱ ሁለንታናዊ ግንባታ ክልሉ ከፌዴራል መንግስት ጋር ተቀናጅቶ በትብብር የሚሠራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ህግን በማስከበሩ ሂደት መረጃን ለህዝብ በማድረስ ለተሳተፉ የኦቢኤን ጋዜጠኞች ዛሬ እውቅና በተሰጠበት ወቅት አቶ ሽመልስ እንዳሉት ጁንታው የኦሮሞ ወጣቶች፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች ጭምር የበላ ነው ።

የተሰጠውን ይቅርታ ወደ ጎን በመተው በንቀት ወደ ክህደት በመግባቱ ራሱን በራሱ የበላ ነው ብለዋል።

ኦቢኤን እንደሌሎች መገናኛ ብዙሃን ሁሉ በዘመቻው ወቅት ከውጭና ውስጥ የተከፈተውን አሉባልታ በማምከን ለህዝብ ትክክለኛ መረጃ መስጠቱን አድንቀዋል።

ኦቢኤን አሁንም ህዝቡን ከድህነት ለማውጣት ሙያዊ በሆነ መንገድ ህዝቡን ማገልገሉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት  ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል።

አሁን አልፈን ከመጣነው ችግር  በላይ ውስብስብ የሆኑ ማነቆዎች ይጠብቁናል፤ ህዝቡን ከድህነት ማላቀቅ፣ በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ራስን ማብቃት፣ የሀገሪቱን ህዝቦች የምትመስል ሀገርና ሥርዓት መገንባት ላይ አሁንም በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

ለሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ ግንባታ ክልሉ ከፌዴራል መንግስት ጋር ተቀናጅቶ በትብብር የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ሽመልስ ኦቢኤን  ገቢ ማመንጨት፣ተጨማሪ የማሰራጫ ጣቢያዎችን በማመቻቸት  ሌሎች ተደራሽ ያልሆኑ ብሔሮችና ቋንቋዎችን ሊያደርስ እንደሚገባ ጠቁመው የክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

ሚዲያው የህዝብ ልሳን እንዳይሆን ጁንታው ሲሰራ ነበር ያሉት ደግሞ የኦቢኤን የቦርድ ሰብሳቢና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ናቸው።

ይህም ሆኖ ኦቢኤን የኦሮሞ ህዝብ አንድነት እንዲጠናከር፣ ባህል፣ ቋንቋና ማንነትን በማሳደግ ረገድ አመርቂ ስራ የሰራ የሚዲያ ተቋም ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ኦቢኤን የኦሮሞ ህዝብ በሀገር ግንባታ የነበረውን ሚና በማጉላት፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልሳን ወደ መሆን የተሻገረ የህዝቦች ድምፅ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ በህግ ማስከበር ዘመቻው በከፍተኛ ዲሲፕሊን ለፈፀሙት ጀግንነት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል ።

አምስት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችና የህፃናት ፕሮግራም በዚህን ዓመት ይከፈታሉ ያሉት አቶ አዲሱ ተቋሙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታጠቅ በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

አሁንም ትክክለኛ መረጃ ለህዝብ የማድረስ ስራ ከሌሎች ጋር ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል።

በትግራይ ክልል በተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለህዝብ በማድረስ ወሳን ሚና የነበራቸው ኢዜአ፣ ኦቢኤን እና ኢቲቪ  ላበረከቱት አስተዋፅኦ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ምስጋና አቅርበዋል።

የክልሉ መንግስትና ድርጅቱ በዘመቻው ለተሳተፉ ጋዜጠኞች  3 ሚሊየን ብር የማበረታቻ ሽልማት መሰጠቱም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም