ኢትዮጵያን ወክለው በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚተፉ አትሌቶች የማጣሪያ ውድድር ተካሄደ

80

ጥር 8/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ወክለው በዚህ ዓመት በቶኪዮ በሚካሄደው ኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች የማጣሪያ ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሄደ።

የማጣሪያ ውድድሩ የተካሄደው ከ800 ሜትር እስከ 10 ሺህ ሜትር ርቀቶችና የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ውድድር በሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ነው።

በእያንዳንዱ ርቀት ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶችም ተመርጠዋል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ አትሌቶች በቅደም ተከተል 10 ሺህ፣ ሰባት ሺህ እና ሶስት ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል።

የኮሚቴው ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚካፈሉ አትሌቶች ልምምዳቸውን በጥሩ ሁኔታ እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዝግጅት የሁለትና የሦስት ወራት እንደነበር አስታውሰው አሁን አትሌቶች ስምንት ወራት ቀደም ብሎ ሆቴል ተይዞላቸው ልምምዳቸውን እየሰሩ እንደሆነ ነው የገለጹት።

ይህ የማጣሪያ ውድድርም  ሆቴል ተይዞላቸው ልምምድ እያደረጉ ከሚገኙ አትሌቶች መካከል የተሻለ አቅም ያላቸውን ለመምረጥ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በማጣሪያው የተመረጡ አትሌቶች የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ለማድረግ ጠንካራ ልምምዳቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ኅብረተሰቡ የኦሊምፒክ ቡድኑን የመደገፍና የማበረታታት ተግባሩን እንዲቀጥልና በሚገኘው ውጤት ላይ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጠይቀዋል።

መንግሥት ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ልዩ ትኩረት በመስጠት ላደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።

ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉና የኦሎምፒክ ኮሚቴው የስራ አስፈጻሚ አባላት በስታዲየሙ ተገኝተዋል።

ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበት የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ዓመት ተራዝሞ በመጪው ክረምት እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም