በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች የነጋዴውን ችግር ማቃለል ተችሏል - የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ

55

ጥር 8/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ለውጡን ተከትሎ በተወሰዱ የአሰራር ማሻሻያ እርምጃዎች የነጋዴውን ችግር ማቃለል መቻሉን የከተማዋ ንግድ ቢሮ ገለፀ።

ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ 100 ሺህ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ ማውጣታቸው ተገልጿል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።   

በውይይቱ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ፣ የነጋዴዎች ፎረም አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የለውጥ ሥራዎች፣ የታዩ ውጤቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ጹሑፍ ቀርቦ ተመክሮበታል።  

ነጋዴው በለውጡ ሂደቱ ስለሚኖረው ሚና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በዘርፉ የሚታየውን ሕገወጥነት መከላከል ጤናማና ሚዛናዊ ውድድር በነጋዴው ዘንድ እንዲጎለብት ማስቻል የመድረኩ ዓላማ መሆኑ ተገልጿል።    

የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ የንግዱ ማኅበረሰብ የሚያጋጥመውን ችግር ለመፍታት በተለይም ከለውጡ ወዲህ በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ብለዋል።   

የአቅርቦት እጥረት አንዱ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው በዚህ ላይ የመፍትሔ እርምጃዎችን ማሳየትና ሕገ-ወጥነትን እንዴት መከላከል ይቻላል? የሚለው የመድረኩ ዓላማ መሆኑን አብራርተዋል።

ነጋዴዎች ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ አሠራሮችን የማቅለል ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው የተለያዩ አዋጆች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል።    

በዚህም ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ 100 ሺህ ነጋዴዎች ንግድ ፈቃድ አውጥተዋል ነው ያሉት።  

ቀደም ሲል 1 ሺህ 500 ፈቃድ መስጫ መደቦች እንደነበሩ የጠቀሱት አቶ አብዱልፈታ ለመደቦቹ ይጠየቅ የነበረው ተገቢ ያልሆነ የብቃት ማረጋገጫ ማሻሻያ ተደርጎበታል ብለዋል።  

ብቃት ማረጋገጫ የሚጠየቅባቸው ፈቃድ መስጫ መደቦች ወደ 52 ዝቅ መደረጉን ከለውጡ በኋላ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ጠቅሰዋል።      

ሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን በተመለከተ ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ አሠራሮች መዘርጋታቸውን በመዲናዋ የሚገኙ የገበያ ማዕከላትም ወደ ዘመናዊነት እንዲቀየሩ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።     

እንደ አቶ አብዱልፈታ ገለጻ ለንግዱ ማኅበረሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ንግድ ፈቃድ በኦንላየን የሚወጣበት ሥርዓት በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል።

በውይይቱ ላይ አስመጪዎች፣ ላኪዎች፣ ጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች እንዲሁም በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም