ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

56

ጥር 8/2013 ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 200 ተማሪዎች አስመረቀ።

ተመራቂዎቹ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የመደበኛና የማታ መርሃ ግብሮች በስድስት የሙያ መስኮች የሰለጠኑ ሲሆኑ 735ቱ ሴቶች ናቸው።

የዩኒቨርሲቲው መስራችና ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር የወንድወሰን ታምራት ምሩቃኑ በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ችግሮችን ለመፍታት በማዋል ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በቁርጠኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል፡፡

ተመራቂዎቹም በስልጠና ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ምሩቃን መካከል በአካውንቲንግና ፋይናንስ የትምህርት ዘርፍ የማዕረግ ተመራቂዋ ሃሌሉያ ሞገስ በዩኒቨርሲቲው ቆይታዋ ተጨባጭ እውቀት መቅሰሟን ተናግራለች።

"ያገኘሁትን እውቀትና ልምድ በመጠቀም ራሴን ይበልጥ ለማሳደግ፣ ኅብረተሰቡንና አገሬንም ለማገልገል ዝግጁ ነኝ" ብላለች፡፡

ሌላዋ የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ሳራ ጁሀር በተማረችበት የሙያ መስክ ለአገርና ለሕዝብ እንደምትሰራና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የበኩሏን እንደምትወጣ ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም