መሪ ዕቅዱ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ካጋጠሙ አሁናዊ ፈታኝ ሁኔታዎች አንጻር መተንተን አለበት - የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር

77

አዲስ አበባ ጥር 8/2013 (ኢዜአ) የጠቅላይ አቃቤ ሕግ የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ካጋጠሙ አሁናዊ ፈታኝ ሁኔታዎች አንጻር መተንተን እንዳለበት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር መከረ።

ማኅበሩ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ ተወያይቷል።

የማኅበሩ ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው የዕቅዱን ምልከታ፣ መታየት፣ መካተትና መስተካከል አለባቸው በተባሉ ነጥቦች ላይ ፅሁፍ አቅርበዋል።

በፅሁፋቸው መሪ ዕቅዱ ያስቀመጣቸውን አዎንታዊ ነጥቦች የዘረዘሩ ሲሆን "በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓት ውስጥ አዳዲስና ዘመናዊ ሃሳቦችን ያካተተ" ብለውታል።

በወንጀል መከላከል፣ በምርመራ፣ በክስና በማረም ሂደት የሚስተዋለውን የሠብዓዊ መብት ጥሰት ዜሮ ማድረስ በዕቅዱ መካተቱንም በበጎ ጎን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ጥራት ያለው የፍትህ ስርዓት ለመዘርጋት በዕቅዱ መታየትና ተተንትነው መቀመጥ አለባቸው የተባሉ ሃሳቦችንም ዘርዝረዋል።

ዕቅዱ የሕገ-መንግስቱን መኖር እንደ መልካም አጋጣሚ፤ አለመተግበሩን እንደ ፈታኝ ሁኔታ ቢያስቀምጥም መተግበር አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ቅቡልነቱና የመሻሻል ሂደቱ ፈተና ይሆናል የሚል እምነት አላቸው።

እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለጻ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ያሉ ሁኔታዎችን በማካተት ሕገ-መንግስቱ የሚሻሻልበትና ተቀባይነቱ የሚጨምርበት ሁኔታ በዕቅዱ መታየት አለበት።

በአሁኑ ወቅት የሕግ የበላይነትን በተግባር ለማስጠበቅ ካጋጠሙ ችግሮች አንጻር ጥልቅ የአሁናዊ ሁኔታ ትንታኔ በዕቅዱ መካተት እንዳለበትም መክረዋል።

ይህም ለችግሩ እውቅና በመስጠት መፍትሄ ለማመላከት የሚያግዝ ሲሆን እንደ ችግር ተመዝግቦ መቀመጡ እንዳይደገም አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ እየተካረረ ያለው የብሔር ፖለቲካ ለሕግ ማስፈጸም ዋነኛ ችግር መሆኑን ጠቁመው ሰነዱ ችግሩን በሚገባ ተንትኖ ማስቀመጥ ይኖርበታል ብለዋል።

በዕቅድ ሰነዱ ላይ የሚነሱ ሃሳቦች ተካተው በትክክል ከተተገበሩ ለመሰል ተቋማት አርዓያ ሊሆን እንደሚችል አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ከሚቀያየረው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የዕቅድ ዓመቱን ወሰን መርዘም በድክመት አንስተው በአጭር ጊዜ ከፋፍሎ መተግበር ይኖርበታል ብለዋል።

ጠንካራ የአቃቤ ሕግ ተቋም መገንባት፣ የሰው ሃይል አቅምን ማሳደግ፣ ተጠያቂነትና ሌሎች በዕቅዱ መታየት አለባቸው የተባሉ ሃሳቦችም ከተሳታፊዎች ተነስተዋል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ አማካሪ አቶ ጥላሁን ወርቁ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የምሑራን፣ የሲቪል ማኀበራትና ሌሎችም ያላቸውን ጉልህ ድርሻ አስረድተዋል።

በ10 ዓመት መሪ ዕቅዱ ላይ በሕግ ባለሙያዎች ማኅበር የተሰጡ ሙያዊ አስተያየቶች በድጋሚ እንደሚታዩም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም