ኮሚሽኑ የ49 ሰዎችን ሕይወት አትርፏል ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትም ከውድመት ታድጓል

114

አዲስ አበባ ጥር 8/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ የእሣትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት ካጋጠሙ የእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች የ49 ሰዎችን ሕይወት ማትረፉንና ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከውድመት መታደጉን ገለፀ።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፋት ስድስት ወራት 121 የእሳት ቃጠሎና 78 ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ተከስተዋል።

ከ199 አደጋዎች መካከል 197ቱ በአዲስ አበባ፤ ሁለቱ ደግሞ በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ነው የተከሰቱት።

የቤት ቃጠሎ፣  የህንፃ መደርመስ፣ ውሃ ውስጥ እና የመፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ መግባት፣ ጎርፍ፣ የተሽከርካሪ ግጭትና ሌሎቹም አደጋዎች ለንብረት መውደምና ለሰው ሕይወት መጥፋት መንስኤ ሆነዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በተከሰቱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ሳቢያ ግምታቸው ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ንብረቶች ሲወድሙ ከ1 ቢሊዮን 411 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ንብረት ማትረፍ ተችሏል።

በአደጋዎቹ ከደረሰው የንብረት ውድመት በተጨማሪ በሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት አጋጥሟል።

ይሁንና ኮሚሽኑ ጉዳቶችን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ርብርብ የሰዎችን ሕይወትና በቢሊዮን የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን አቶ ጉልላት ተናግረዋል።

አቶ ጉልላት በበጀት ዓመቱ በስድስት ወራት ያጋጠሙት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ከ2012 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር መቀነሱን ገልፀዋል።

ባለፈው ዓመት በስድስት ወራት 137 የእሳትና 112 ድንገተኛ አደጋዎች ሲከሰቱ፤ ዘንድሮ 121 የእሳትና 78 ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ናቸው የተከሰቱት።

አደጋን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የመንገዶች መጨናነቅ እንቅፋት የሚሆንበት አጋጣሚ መፈጠሩን አስታውሰው በዚህ ሳቢያ ለአንዳንድ አደጋዎች ፈጥኖ ምላሽ መስጠት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

ይህ እንዳይሆን የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ተሽከርካሪዎች ድምፅ እያሰሙ ወደ አደጋ ስፍራ ሲጓዙ ሌሎች ተሽከርካሪዎች በቻሉት መጠን ቅድሚያ በመስጠት እንዲተባበሩ አቶ ጉልላት ጥሪ አቅርበዋል።

አደጋዎችን  የመከላከል ኃላፊነት የሁሉም መሆኑን ጠቁመው ኅብረተሰቡም ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ለጉዳት እንዳይጋለጥ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው በስድስት ወራት የደረሱ አደጋዎችን ለመከላከል 354 ማሽነሪዎችና 20 አምቡላንሶች አገልግሎት ላይ ውለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም