ኦቢኤን መረጃዎችን በሀገሪቱ 13 ቋንቋዎች በማሰራጨት የህዝቡን አቃፊነት በተግባር ማሳየቱን አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ

96

አዳማ ጥር 8/2013 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ብርድ ካስቲንግ ኔትወርክ/ ኦቢኤን/ መረጃዎችን በሀገሪቱ 13 ቋንቋዎች በማሰራጨት የኦሮሞን ህዝብ አቃፊነት ያሳየና ኢትዮጵዊነትን በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።

በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ለተሳተፉ የኦቢኤን ጋዜጠኞች ዛሬ በአዳማ እውቅና በተሰጠበት ወቅት ከተገኙት መካከል የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ፍሰት ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት በህግ ማስከበሩ ዘመቻ በጋዜጠኞች ዘንድ የታየው ቁርጠኝነት እጅግ የሚደነቅ ነው።

ኦቢኤን መረጃዎችን በሀገሪቱ 13 ቋንቋዎች በማሰራጨት የኦሮሞን ህዝብ ትልቅነትና አቃፊነት ያሳየ ከመሆኑም ባለፈ ኢትዮጵያዊነት የተንፀባረቀበት ነው ብለዋል ።

ህዝቡ ይበልጥ የተቀራረበበትና አንድ የሆነበት ሃሳብን በተግባር ማሳየቱን የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን አሁን ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻል ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው ኦቢኤን ሁሉንም በማቀፍ ኢትዮጵያዊነትን በተግባር ያስመሰከረ ነው ብለዋል ።

መረጃ ተደራሽ መሆን አለበት ሲባል ህዝቡ በሚገባው ቋንቋ እንደሆኑ ጠቅሰው ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ይህን መከተል እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ኦቢኤን በዘመቻው ከሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተና ህዝቡ ትክክለኛ መረጃ ስለዘመቻው እንዲያገኝ ያስቻለ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በስራዎች ላይ የተቀናጀ የመገናኛ ብዙሃን ሥራና ትብብር የታየበት ነው ያሉት ደግሞ የሀገር መከላከያ የሚዲያና ኢንዶክርነሽን ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ሙሐመድ ተሰማ ናቸው።

ጋዜጠኞቹ በማህበራዊ የትሥሥር ገጾች የነበረውን ብዥታ ያፀዱና ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖራቸው በጀግንነት ብቻ ብቃታቸውን ማሳየታቸውን ተናግረዋል ።

የተሰጣቸውን ህዝባዊ ሃላፊነት በብቃት የተወጡ በመሆኑ ክብር የሚገባቸው ናቸው ብለዋል ።

የኦሮሚያ መንግስትና ህዝብ ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ርብርብ ለህግ ማስከበሩ ዘመቻ መሳካት ወሳኝ ሚና እንደነበራቸው ጠቅሰዋል።

ኦቢኤን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልሳን ነው ያሉት ደግሞ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት ናቸው።

በ13 የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች በማሰራጨት ለህዝቦች ድምፅ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተለይ ጁንታው በህዝቦች መካከል መጠራጠር እንዲኖርና ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ዕድሜውን ለማረዘም ያደረገውን ጥረትና አሉባልታ በማክሰም ዛሬ ለተደረሰበት ደረጃ መብቃት መቻሉን አውስተዋል።

ድርጅቱ የህዝብ ልሳን እንዳይሆን ጭምር ሲያደረግ የነበረውን ጫና በመቋቋም ዛሬ በጁንታው ላይ የተወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ በግንባር ቀደምትነት ለኢትዮጵያ ህዝብና ለዓለም በማድረስ የጥፋት ቡድኑ ውድቀት እንዲፋጠን የድርሻውን መወጣቱን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

አሁንም የህዝቦች ልሳን በመሆን ለእኩልነት፣ ነፃነት፣ ዴሞክራሲና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በሙሉ አቅማችን እንሰራለን ብለዋል ።

በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ለተሳተፉ 28 የኦቢኤን ጋዜጠኞች የደመወዝ ጭማሪና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም