ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ለማጽደቅ ዝግጁ ናት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

90
አዲስ አበባ ግንቦት 6/2010 ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ለማጽደቅ ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጠቆሙ። ኢትዮጵያ ያከናወነችው መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማትና የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ አገሪቱን ምቹ የቢዝነስ መዳረሻ እንዳደረጋት ተናግረዋል። እ ኤ.አ በመጋቢት ወር 2018 በርዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ 44 የአፍሪካ አገሮች የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጣና እውን ለማድረግ የተፈራረሙ  ሲሆን፤ ኬኒያና ጋና ስምምነቱን ያጸደቁ ቀዳሚ አገሮች መሆን ችለዋል። የአፍሪካ አገሮች የፋይናንስና፣ የኢኮኖሚ ልማትና የእቅድ ሚኒስትሮች ጉዳዩን በሚመለከት በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ውይይት እያደረጉ ነው። ውይይቱ ከሁለት ቀን በፊት በባለሙያዎች ደረጃ የተጀመረ ሲሆን፤ ዛሬ በሚኒስትሮች ደረጃ ምክክር እየተደረገበት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ውይይቱን በይፋ ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ በአህጉሪቱ ነጻ የንግድ ቀጠና እውን መሆን ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠርና አብሮ ለማደግ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ኢትዮጵያ የጋራ ነጻ የንግድ ቀጣናን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በመገንዘቧ ስምምነቱን ለማጽደቅ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማቷን ለመደገፍ መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማትንና የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እንዳከናወነች ዶክተር አብይ ተናግረው፤ ይህም አገሪቱን ተመራጭ የቢዝነስ መዳራሻ እያደረጋት መሆኑን ጠቁመዋል። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ሲተገበርም ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የመሳብ እድሏ እንደሚጨምር አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም