በአራት ክልሎች የሚደረገው የአቅም ማጎልበት ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል...ሠላም ሚኒስቴር

91

አሶሳ፤ ታህሳስ 08/ 2013(ኢዜአ)የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋር እና ሱማሌ ክልሎችን አቅም በማጎልበት እምቅ የተፈጥሮ ሃብታቸው በአግባቡ እንዲለማ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉን የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የልማት ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያግዝ የአሠልጣኞች አቅም ግንባታ ሥልጠና በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡

ሥልጠናው ትናንት ሲጀመር በሠላም ሚኒስቴር የፌደራል እና ልዩ ድጋፍ ዳይሬክተር ጀኔራል ፕሮፌሰር ደገፋ ቶሎሳ ለኢዜአ እንዳሉት ክልሎቹ  እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ያላቸው ናቸው።

ይሁንና ክልሎቹ ሃብታቸውን ለድህነት ቅነሳ በማዋል ረገድ አሁንም ክፍተቶች አሉባቸው ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በተለይ ከለውጡ በኋላ አቅማቸውን በሚገባ አጎልብቶ  ሃብታቸውን በማልማት ከራሳቸው አልፎ  ለሃገር ኢኮኖሚ እንዲውል የተጠናከረ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰር ደገፋ ገለጻ ሠላም ሚኒስቴር ድጋፉን እያደረገ የሚገኘው ከውሃ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ መስኖ ፣ ኢነርጂና  ሲቪል ሰርቪስና ሌሎችም  የፌደራል መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ነው፡፡

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች በበጀት ጭምር  እገዛ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አዎንታዊ የመንግስታት ግንኙነት እና ልማት ከሠላም ጋር ያለውን ቁርኝት የሚያጎለብቱ ተግባራትም እንዳሉ ፕሮፌሰሩ አመላክተዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ባባክር ከሊፋ በበኩላቸው በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ለሃገር ኢኮኖሚ እንዲውል በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጀመሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በክልሉ ወርቅ በባህላዊ መንገድ በስፋት ቢመረትም አምራቾቹ የምግብ ዋስትናቸውን በሚገባ በማረጋገጥ ከድህነት መውጣት አልቻሉም ብለዋል፡፡

ለሃገር ኢኮኖሚ በሚገባ አስተዋጽኦ እያደረገ እንዳልሆነም የገለጹት አቶ ባበክር የችግሩ ምክንያት ደግሞ የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህል አለመዳበር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ስትራቴጅክ እቅድ መነደፉን ጠቁመዋል፡፡

ከፌደራል መንግስት የሚገኘውን ልዩ እገዛ ጭምር በመጠቀም እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰው፤ በተለይ የቁጣባ ልምድ እንዲዳብር የአመራሩን አቅም በማጎልበት ወደ ስራ ለመግባት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ለአራት ቀናት በሚቆየው የሥልጠና  መድረክ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ200 የሚበልጡ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም