የከተራና የጥምቀት በዓላት የኮቪድ-19 መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር ይከበራሉ - የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን

175

አዲስ አበባ ጥር 8/2013 (ኢዜአ) ሕዝበ ምዕመኑ የከተራና የጥምቀት በዓላትን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር እንዲያከብር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አሳሰበች።

የከተራና የጥምቀት በዓላት በመላው ኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ጥር 10 እና 11 ቀን ይከበራሉ፤ በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ ደግሞ ከዕምነቱ ተከታዮች ባሻገር የበርካታ አገራት ጎብኚዎች፣ ዲፕሎማቶችና እንግዶች የሚታደሙበት በመሆኑ በተለየ ድምቀት ነው የሚከበረው።

ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዞ በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ የተጠመቀበትን ዕለት በማሰብ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው።

የዕምነቱ ተከታዮች በዓሉን ከዋዜማው ከተራ ጀምሮ በተለያዩ ኃይማኖታዊና ባሕላዊ ስነ-ስርዓቶች ያከብሩታል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ  የከተራና የጥምቀት በዓላትን ለማክበር እየተደረገ ስላለው ዝግጅትና ኮቪድ-19ን ለመከላከል መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ለኢዜአ ገልጸዋል። 

ዘንድሮ በዓላቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መወሰድ ያለባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች ተግባራዊ በማድረግና ለሰዎች ጤና በመጠንቀቅ የሚከበር ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ አካላዊ ጥግግትን ለመቀነስ ፒያሳ የነበረውን የአትክልት ተራ ግብይት ወደ ጃንሜዳ አዛውሮት እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና ስፍራው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ በመሆኑ በጃንሜዳ ሲሰሩ የቆዩ ነጋዴዎች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ ወደተገነባው የአትክልት ገበያ ስፍራ እንዲዛወሩ አድርጓል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ታህሳስ 8 ቀን 2013 ዓ.ም የጃን ሜዳ የታቦት ማደሪያን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማትያስ ማስረከባቸውም አይዘነጋም።

የከተማ አስተዳደሩ ላደረገው ትብብር ምስጋና ያቀረቡት ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያኗ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ስፍራውን ተረክባ በወጣቶች አማካኝነት የፅዳትና ማስዋብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

ገዳማትና አድባራትም የከተራና የጥምቀት በዓላት በደመቀ ሁኔታ እንዲከበሩ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በዓሉ ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር ቤተክርስቲያኗ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ጨምሮ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋራ በመሆን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጓንም ብፁዕነታቸው አስታውቀዋል።

ሕዝበ ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድና ለበዓሉ ሠላማዊ ሆኖ መከበር የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በከተራና በጥምቀት በዓላት ዲፕሎማቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ቱሪስቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሠላም፣ የጤና የደስታ እንዲሆን ተመኝተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ታሕሳስ 2012 ዓ.ም የጥምቀትን በዓል በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስነት መዝግቦታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም