በደቡብ ወሎ 105 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬትን በበልግ ለማልማት የእርሻ ሥራ እየተካሄደ ነው

79

ደሴ፤ ጥር 08/2013 (ኢዜአ) በተያዘው የበልግ ወቅት 105 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያየ ሰብል ለማልማት የእርሻ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጹ፡፡

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት የበልግ እርሻ ሥራ እየተካሄደ ያለው በዞኑ በልግ አብቃይ በሆኑ 15 ወረዳዎች ውስጥ ነው።

በበልግ ልማቱ 200 ሺህ ያህል አርሶ አደሮች በመሳተፍ የእርሻ ማሳቸውን እስከ ሦስት ጊዜ ደጋግመው በማረስ ለዘር እያዘጋጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በተያዘው ወር ር መጨረሻ የዘር ስራውን ለማስጀመርም የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አንድ ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያና 25 ሺህ ኩንታል ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንዲውል መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በበልግ ልማቱ በዋናነት የአገዳና የጥራጥሬ ሰብል  እንደሚለማ ጠቁመው፤ ከሚለማው መሬት ከአንድ ሚሊዮን  600 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

በደሴ ዙሪያ ወረዳ የ041 ቀበሌ  አርሶ አደር አደም ሸህ ሙሄ በሰጡት አስተያየት አንድ ሄክታር ማሳቸውን በበልግ ጤፍና ገብስ ለማልማት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

በወሩ  መጨረሻ ዘር ለመጀመር ማሳቸውን ደጋግመው እያረሱ መሆናቸውን  ጠቁመው፤ የግብርና ባለሙያዎች እየደገፏቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በየዓመቱ የበልግ ወቅት ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን በተለያየ የሰብል ዓይነት ሲያለሙ መቆየታቸውን ያስረዱት ደግሞ  የለጋአምቦ ወረዳ አርሶ አደር ጀማል አብደላ ናቸው፡፡

ዘንድሮም በዚሁ ማሳ ላይ ስንዴ፣ ገብስና ጤፍ በመዝራት ለማልማት መሰናዳታቸውን ገልጸዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ዓመት የበልግ ወቅት 104 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በማልማት ከአንድ ሚሊዮን 400ሺህ  ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም