የመንግስት አገልግሎት ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ

146

አዳማ፤ ጥር 07/2013 ( ኢዜአ) የመንግስት አገልግሎት ዘርፉን በማዘመን የለውጥ ፕሮግራሞች በነፃ፣ገለልተኛና ብቁ የሰው ሃይል እንዲመራ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገለጸ።

ፍኖተ ካርታውን በግብዓት ለማዳበርና በአፈፃፀም ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ማነቆዎችን ከወዲህ ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ ለማስቀመጥ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

በዚህ ወቅት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ የመንግስት የአገልግሎት ዘርፉን በማዘመን የሴክተሮች የለውጥ ፕሮግራሞች በነፃ፣ገለልተኛና ብቁ የሰው ሃይል እንዲመራ ለማስቻል ነው።

ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች፣አሰራር የመዘርጋትና አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር  ጭምር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ ነፃ፣ገለልተኛና ያለአድሎ ብቃቱ የማያጠራጥር የሰው ሃይል ብቻ እንዲመራና ሀገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ እንደሆነም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

መድረኩ የተሰናዳውም ዘርፉን ለማዘመን የተዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ በግብዓት ለማዳበርና በአፈፃፀም ወቅት ሊያጋጥም የሚችሉ ማነቆዎችን ከወዲህ  ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ብለዋል።

ፍኖተ ካርታው የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪካዊ ዳራን የቃኘ ፣  ነበራዊ ሁኔታዎችንና ቀጣይ የታሰበውን የቢሮክራሲ ግንባታ የሚደርስበትን ያስቀመጠ ነው ያሉት ደግሞ በእንግሊዝ ሀገር በመንግስት ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ ያሉና በመድረኩ ላይ ጹሑፍ ያቀረቡት ዶክተር ግርማ ኤጄረ ናቸው።

የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታው ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው፤ እኔ በዝግጅቱ ስለተሳተፍኩ ሳይሆን ጠንካራ ተቋማትና ሀገረ መንግስት የገነቡ ከ26 በላይ ሀገራት ተሞክሮ ያካተተ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ዶክተር ግርማ ከመንግስት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ፈፃሚዎች ለፍኖተ ካርታው ተግባራዊ መሆን መረባረብ እንዳለባቸውም  አመልክተዋል።

ለፍኖተ ካርታው ውጤታማነት  የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር የመንግስት አገልግሎት እንዲሻሻልና እንዲለወጥ መስራት አለባቸው ብለዋል።

በሀገሪቱ የቡድኖችና ግለሰቦች ጥንካሬ እንደነበር አውስተው ብዙን ጊዜ የሚወጡ ፖሊሲዎችና እቅዶች ተፈፃሚነት የማይኖራቸው ጠንካራ ተቋማት ባለመኖራቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ፍኖተ ካርታው ይህን ችግር ከመሰረቱ በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እውን የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።

የሐረር ክልል የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ሁንዴ በበኩላቸው አሁን ያለውን የአገልግሎት አሰጣጣችን በትክክል ለመፈተሽ ፍኖተ ካርታው ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

በዚህ የተካተቱ ፕሮግራሞች የመንግስት አገልግሎት ሞዴልና ብቃት ባለው የሰው ሃይል እንዲመራ የሚያስችል ከመሆኑንም ባለፈ ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ስራዎች በማስቀጠል ረገድ የላቀ ሚና እንደሚኖረው  ተናግረዋል።

ፍኖተ ካርታው አሁን ያለውን ነበራዊ ሁኔታና አዲሱን የሀገረ መንግስት ግንባታ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ካሣ አበባው ናቸው።

ነፃ፣ ከአድሎ የፀዳ  የመንግስት አገልግሎት እንዲረጋገጥና ለተገልጋዩ  ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ከአስርም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች  የመጡ የዘርፉ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም