የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሠላም እንዲከበሩ እንሰራለን - የአዲስ አበባ ወጣቶች

76

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) የከተራ እና የጥምቀት በዓላት አከባበር ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ አካላት ጋር እንደሚሰሩ የመዲናዋ ወጣቶች ተናገሩ።

ወጣቶቹ መጪውን የከተራና የጥምቀት በዓላት አከባበር አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ "በከተማችን የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት ሠላማዊ ሆነው ይጠናቀቁ ዘንድ እንሰራለን" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተካሄደው።

በመድረኩ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደ ከተማ የነበሩ ፈተናዎችን ወጣቱ ባደረገው ርብርብ ለማለፍ እንደተቻለ ተነግሯል።

የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ቴዎድሮስ ተስፋዬ የከተራና የጥምቀት በዓላት በሠላም እንዲከበሩ የወጣቱ ሚና ጉልህ መሆኑን አስታውሷል።

"በዓሉ በሠላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብረው ከመስራት ባለፈ የጸጥታ ችግሮች ሲያስተውሉ ለሚመለከተው አካል በፍጥነት ማሳወቅ ይኖርባቸዋል" ብሏል።

ወጣት አብይ ጥላሁንም ጥምቀት በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት አንዱ እንደመሆኑ ኅብረተሰቡ ያለምንም ስጋት በዓሉን ማክበር እንዲችል እርሱና ጓደኞቹ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግሯል።

በበዓላቱ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት የማስተባበር ስራ ለሚሰሩ የከተማዋ ወጣቶች የመለያ ባጅ እና አንጸባራቂ ልብስ እንደተዘጋጀላቸው ገልጿል።

"በዓሉ በሠላም እንዲከበር ከመስራት ባሻገር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል ማክበር ይገባል" ያለችው ደግሞ ወጣት ዘረዋ መለሰ ናት።

በዓሉ በርካታ ሰዎች የሚታደሙበትና በአደባባይ የሚከበር እንደመሆኑ ኅብረተሰቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መዘንጋት እንደሌለበት አመልክታለች።

"የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያዊያን ሠላም ወዳድና እንግዳ ተቀባይ መሆናችንን ለዓለም የምናሳይበት መድረክ ነው" ብላለች።

በዓሉ ሲከበር ከማስተባበር ባለፈ አላስፈላጊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ለጸጥታ አካላት ፈጥኖ በማሳወቅ ለመፍትሄ እንደሚሰሩም ነው ወጣቷ የገለጸችው።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዳይሬከተር ኮማንደር ሰለሞን ፋንታሁን በበኩላቸው በዓሉ በሠላማዊ ሁኔታ እንዲከበር ወጣቶች እንደ ከዚህ ቀደሙ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ጸረ ሠላም ኃይሎች በዓሉን ለፍላጎታቸው መጠቀሚያ እንዳያደርጉት ወጣቶች ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው አካባቢያቸውን በንቃት እንዲጠብቁም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም