በሐረሪ ክልል ኮሮናን ከመከላከል አንጻር እየተስተዋለ ያለውን መዘናጋት ለማስተካከል መሥራት አለበት... አቶ ኦርዲን በድሪ

50

ሐረር ፤ ጥር 07/ 2013( ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የኮሮና ቫይረስን ከመከላከሉ አንጻር እየተስተዋለ ያለው መዘናጋት ለማስተካከል ሁሉም አካል በትኩረት መሥራት እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡

በክልሉ የኮሮና  ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት የሚተገበር የንቅናቄ ማብሰሪያ  መድረክ በሐረር ከተማ ተካሄዷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ ብሎም ክልሉ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል  ህዝብና መንግስት ርብርብ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ለዚህም የሀይማኖት አባቶች፣ ሀገር ሽማግሌዎችና እድሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅትም ቀደም ሲል የተጀመሩ መልካም ተግባራትን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ ቀደም ሲል ህብረተሰቡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል  አጠቃቀም መልካም የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት መዘናጋትና መቀዛቀዝ እንደሚስተዋል አስረድተዋል።

በተለይም በገበያ ፣ ትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ አካባቢዎች ጭንብል  ከመጠቀም፣ ርቀትን እና ንፅህናን ከመጠበቅ አኳያ  ክፍተቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡

ይህንን ክፍተት ለማስተካከል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች  ለማጎልበትና የወጡ መመሪያዎችን ለማስተግበር  ሁሉም አካል በትኩረት መሥራት እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው በንቅናቄ ሥራው ቀደም ሲል የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን ማጎልበትና ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ቫይረሱን ከመከላከል አንፃር ከአመራሩ ጀምሮ እየታየ ያለው መዘናጋት መታረም እንደሚኖርበትም

አመልክተዋል፡፡

በተለይም ህዝብ በሚበዛባቸው አገልግሎት መስጫ አካባቢዎች  ልዩ ጥንቃቄና ትኩረት መስጠት  እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱጀባር መሐመድ ናቸው፡፡

የክልሉ  ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብሳ ኢብራሂም  ባለፉት ወራት የቫይረሱን ስርጭት በመከላከል በኩል  ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

ሆኖም በአሁኑ ወቅት በክልሉ ህዝቡ ዘንድ የመዘናጋትና  ቸልተኝነት ችግር እየተስተዋለ በመሆኑ ይህንን ለማስተካከል  በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በንቅናቄ ማብሰሪያ መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ፣ ሀይማኖት አባቶች፣ ሀገር ሽማግሌዎች፣ የእድር መሪዎችና ሌሎችም አካላት  የተሳተፉ ሲሆን በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም